Logo
News Photo

የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር በሽታን አስመልክቶ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ተሰጠ፡፡

የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት በማህፀን በር ጫፍ ካንሰር በሽታ ዙርያ ለድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ሴት ሰራተኞች እና ከተለያዩ የድሬዳዋ አስተዳደር መስሪያ ቤቶችና የሴት አደረጃጀቶች ለተውጣጡ ሴቶች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥቷል፡፡

በስልጠናው መክፈቻ ላይ የተገኙት የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሰለሞን ዘሪሁን ሲሆኑ በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለፁት በአሁኑ ወቅት በሀገራችን በከፋተኛ መጠን እየጨመረ የመጣውን የማህፀን በር ካንሰር በሽታን ለመቀንስና ለመከላከል በሀገር አቀፍ ደረጃ ሰፊ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቁመው ከዚህ ውስጥም  አንዱና ዋነኛው ለበሽታው ተጋላጭ የሆኑ እድሜያቸው ከ14 ዓመት በላይ የሆኑ ሴቶች ስለ በሽታው ያላቸውን ግንዛቤ የማሳደግ ስራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

ዶ/ር ሰለሞን የዛሬው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናም ዩኒቨርሲቲው ይህንኑ መነሻ በማድረግ ያዘጋጀው መሆኑን ገልፀው የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር በሽታን ለመከላካል ሁላችንም ኃላፊነት ስላለብን በሽታው ስር ሰዶ የከፋ ጉዳት ከማስከተሉ በፊት አስቀድሞ መከላከልና ማዳን የሚቻል በመሆኑ ስለ በሽታው ግንዛቤ ያላቸው ሁሉ ግንዛቤው ለሌላቸው በማካፈል የበኩላቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ሥልጠናውን የሰጡት በዩኒቨርሲቲው የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መምህርና በድል ጮራ ሆሲፒታል የማህፀንና ፅንስ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ታፈሰ ደጀኔ ሲሆኑ ስልጠናውም የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ምንነት፣ ምልክቶቹ፣ ህክምናውና የመከላካያ መንገዶቹ ላይ ያተኮረ ነበር፡፡

በመጨረሻም ስልጠናውን የወሰዱ ሰልጣኞች ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ወቅት አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን የማህፀን በር ካንሰር በሽታ ላይ ይህን መሰል ስልጠና ስለሰጣቸው አመስግነው ይህ ስልጠናም በቀጣይ ለሴት የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች እና ጉዳዩ ለሚመለከታቸው የማህበረሰብ ክፍሎች በሙሉ እንዲሰጥ ጠይቀዋል። በተጨማሪም ሰልጣኞቹ እንደማህፀን በር ካንሰር ሁሉ ሌሎች አሳሳቢ እየሆኑ የመጡ በሽታዎች ላይም ዩኒቨርሲቲው መሰል የግንዛቤ ማሰጨበጫ ስልጠናዎችንም እንዲያዘጋጅላቸው ጠይቀዋል።

Share This News

Comment