Logo
News Photo

18ኛው ዓለም አቀፍ ሙስናን የመከላከል ቀን በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በፓናል ውይይት ተከበረ

በአለም አቀፍ  ደረጃ ለ18ኛ ጊዜ በሀገራችን ደግሞ ለ17ኛ ጊዜ እየተከበረ የሚገኛው የፀረ-ሙስና ቀን በዓል ዘንድሮ  "በስነ ምግባር የታነፀ አመራር ከሙስና ለፀዳች ኢትዮጵያ" በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል፡፡


ይህን ቀን በማስመልከት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የፓናል ውይይት በማዘጋጀት የፀረ-ሙስና ቀንን ያከበረ ሲሆን በዚሁ በዓል ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም እንደገለጹት የሙስና ወንጀል ሀገርን ለከፋ የኢኮኖሚ ውድቀት ይዳርጋል፥ በተለይም በመልማት ላይ ባሉ ድሀ ሃገራት ያለንን ውሱን ሃብት ከሙስናና ብልሹ አሰራር ጠብቀን ልማታችን በማስቀጠል እድገት ማስመዝገብ ካልቻልን ህልውናችን አደጋ ላይ ስለሚወድቅ ሙስናን እና ብልሹ አሰራርን የመዋጋት ተግባር ለተወሰ አካል ብቻ የተሰጠ ባለመሆኑ ሁላችንም ተረባርበን ልናስወግደው ይገባል በማት አስገንዝበዋል፡፡


በዩኒቨርሲቲያችን ሙስናንና ብልሹ አሰራርን ለማስወገድ መላው ማህበረሰብ ግንዛቤ ከማሳደግ አንስቶ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን ዶ/ር ኡባህ አንስተው በተደጋጋሚ ጊዜ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ሃብት ያለአግባብ ሲባክን እኔን አይመለከተኝም በሚል ስሜት ኃላፊነትን ያለመወጣት ችግሮች ጎልተው ስለሚታዩ እነዚህን ብልሹ አሰራሮች በመዋጋት በኩል ሁሉም የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በባለቤትነት ስሜት የበኩሉን ይወጣ ዘንድ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡


በድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና መከታተያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሄኖክ አየለ በፓናል ውይይቱ ላይ ተገኝተው እነዳሉት ዳይሬክቶሬቱ ሙስናንና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል በ2013 ዓ.ም ጅምር ቢሆንም  ውጤታማ የሆኑ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቅሰው በተለይም ሙስናን ለመከላከል ትልቅ እገዛ የሚኖረው የሃብት ማስመዝገብ ስራ የተከናወነ ሲሆን በዚህም 2ሺህ 9 መቶ የዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች፣ መምህራን እና የአሰተዳደር ሠራተኞች ሃብትን በመመዝግብ ተጠያቂነት እንዲሰፍን ጥረት ተደርጓል ብለዋል፡፡


አቶ ሄኖክ አክለው የሃብት ምዝገባ በሚከናወንበት ወቅት ሃሰተኛ መረጃ መስጠት እና ሙስና ሲፈፀም ለሚመለከተው አካል ከማጋለጥ ይልቅ በዝምታ የማለፍ ሁኔታዎች በስፋት መስተዋላቸው ሙስናንና ብልሹ አሰራርን ለማስወገድ በሚደረገው ጥረት ላይ ማነቆ እየፈጠረበት ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ሙስናና ብልሹ አሰራር ለመቀነስ የሚያደርገውን ጥረት ስኬታማ ማድረግ እንዲቻልም መላው የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ሙስና በመጠየፍና ተፈፅሞ ሲገኝም በመጠቆም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡

 

በእለቱ ሙስናን አስመልክቶ በፓናል ውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል የጥያቄ እና መልስ ውድድር የተካሄደ ሲሆን ሙስናን በመዋጋት ኃላፊነታቸውን ለተወጡ የአስተዳደር ሠራተኞች ሽልማት ተበርክቷል፡፡ 

Share This News

Comment