የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ እና የሐረርጌ ካቶሊክ ጽ/ቤት ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የተለያየ የልማት ስራዎችን ከዚህ ቀደም የሰሩ ሲሆን ይህንኑ የትብብር ስራበማስቀጠል 100 ስራ አጥ ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ስልጠና ለመስጠት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል። በልብስ ማቅለም እና በሳሙና አመራረት ላይ ትኩረቱን አድርጎ በሚሰጠው ስልጠና ላይ ከተለያዩ የምስራቅ እና ምዕራብ ሐረርጌ ወረዳዎች የተወጣጡ ወጣቶች እንደሚሳተፉበት ተጠቁሟል።
በስምምነት ስነ-ስርዓቱ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ምርምር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ተማም አወል እንደተናገሩት ‘’ከዚህ ቀደም በሁለቱ ተቋማት መሰል ትብብር የሰለጠኑ አብዛኞቹ ወጣቶች የራሳቸውን ስራ መፍጠር ከመቻላቸውም በላይ በተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ ተቀጥረው በመስራት የገቢ ምንጭ መፍጠር እንደቻሉ ተናግረዋል።
የሐረርጌ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ፅህፈት ቤት ዳይሬክተር ዶ/ር ጎሳ መንግስቱ በበኩላቸው ጽ/ቤታቸው በርካታ ማህበረሰብ ተኮር የልማት ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ጠቁመው በተለይ ስራ አጥ ወጣቶች እና የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የስራ ክህሎት ስልጠና በሰፊው እየሰጡ መሆኑን ጠቁመዋል።
100 ወጣቶችን በልብስ ማቅለም እና ሳሙና አመራረት ላይ ተግባራዊ ስልጠና የሚወስዱ ሲሆን ለስልጠናው ከሚያስፈልገው በጀት ውስጥ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ 26.8 % ወይም 695,000 ብር እንዲሁም የሐረርጌ ካቶሊክ ጽ/ቤት 73.2% ወይም 1.895,795 ብር ወጪ እንደሚያደርጉ በመድረኩ ላይ ተጠቁሟል።
Share This News