Logo
News Photo

ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ለሀገር መከላከያ

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች የሃገርን ህልውና ለማስቀጠል ተጋድሎ በማድረግ ላይ ለሚገኘው የመከላከያ ሠራዊታችን የአንድ ወር ደሞዛቸውን በድጋፍ መልክ አበረከቱ፡፡
።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች እና የካውንስል አባላት በተገኙበት በዩኒቨርሲቲው ስታዲየም በተዘጋጀውና በተካሄደው ወቅታዊ ሃገራዊ ሁኔታ ላይ ለመወያየት የተሰባሰቡት የዩኒቨርሲቲው መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች ከገንዘብ ድጋፉ በተጨማሪ በማንኛውም መልኩ ለሃገራቸው መስዋትነት ለመክፈል መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል፡፡
በዚሁ ወቅት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ተወካይ እና የምርምርና የማህበረሰብ አገልግልት ም/ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶክተር ሰለሞን ዘሪሁን እንዳስታወቁት የመማር ምስተማሩ ሂደትም ሆነ እያንዳንችን የእለት ተዕለት ህይወታችንን መግፋት የምንችለው የተረጋጋችና ሰላማዊ አገር ስትኖር መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓትም የሃገራችን እድገትና ብልጽግና የማይጥማቸው በጥፋት መስመር የተሰለፉ የውስጥም ሆነ የውጪ ኃይሎች ሰላማችንን በመንሳት ከመቼውም ጊዜ ይልቅ እኩይ አጀንዳቸውን አንግበው ህልውናችንን በመፈታተን ላይ በመሆናቸው ጠቅሰው ሁላችንም ልዩነታችንን ወደ ጎን በመተው በአገራችን ጉዳይ ላይ ተመሳሳይ አቋም በመያዝ የተጋረጠውን አደጋ ለመቀልበስ በተባበረ ክንድ መመከት ይኖርብናል፡፡
በተለይም በሰሜኑ የሃገራችን ክፍል ከገጠማት የህልውና አደጋ ለመታደግ ውድ ዋጋ እየከፈለ ለሚገኘው የመከላከያ ሠራዊታችን የሚደረገው ድጋፍና አጋርነት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡
በዚሁ ውይይት ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካል ሳይንስና የአለም አቀፍ ግንኙነት መምህርና ተመራማሪ የሆኑት አቶ ሱራፌል ጌታሁን በበኩላቸው በአሁኑ ሰዓት ሃያላን ከሚባሉት አገሮች ሳይቀር እየደረሰብን ያለውን ጫናን ለመቋቋም ሁላችንም በአገራችን ጉዳይ ላይ አንድ አይነት አቋም ይዘን የመጣውን ጫና በመቃወምና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ እውነታውን እንዲያውቅ በማድረገግ በኩል የቻልነውን ሁሉ መወጣት ይገባናል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
በመጨረሻም የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች የእንድ ወር ደሞዛቸውን ለጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችን በድጋፍ መልክ ያበረከቱ ሲሆን የደም ልገሳም አድርገዋል፡፡

Share This News

Comment