Logo
News Photo

የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ባለስልጣን በኤሌክትሮኒክስ የመንግስት ግዥ ሲስተም አጠቃቀም ዙሪያ ግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ፡፡

የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ባለስልጣን ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በድሬዳዋ እና አከባቢው ለሚገኙ የንግዱ ማህበረሰብ የመንግስት ግዥ  በኤሌክትሮኒክስ ሲስተም አጠቃቀም ዙሪያ በዩኒቨርሲቲው የመሰብሰቢያ አዳራሽ በዛሬው እለት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡  

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም በስልጠና መድረኩ ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈው የኤሌክትሮኒክስ  ሲስተም እውን መሆን ዩኒቨርሲቲያችን ተጠቃሚ እንደሚያደርገው ገልጸው በቴክኖሎጂ በመታገዝ ከመደበኛ የግዥ አሰራር ወደ ኤሌክትሮኒክ የግዥ ሂደት በሙሉ አቅም መጠቀም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ  ወ/ሮ ሙሉካ መሀመድ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር አድርገዋል፡፡ ወ/ሮ ሙሉካ በንግግራቸው የዚህ ሲስተም ጠቀሜታው ዘርፈ ብዙ መሆኑን ገልጸው ከሙስና ጋር ያለው አካላዊ ንክክ የሚያስቀር፣ ፍትሃዊነት በተሞላ አሰራር ስራዎችን ማከናወን ማስቻሉ፣ አለማቀፋዊነት ያለው ሲስተም በመሆኑ ከየትኛውም የአለም ክፍል ሆነው መወዳደር ማስቻሉ፣ ጊዜና ወጪ ቆጣቢ በመሆኑ ሲስተሙን ስራ ላይ ማዋል አማራጭ የሌለው መሆኑን አንስተዋል፡፡

በመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሃጂ ኢብሳ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ እየተተገበረ የሚገኘው የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ (Electronic Government Procurement e-GP)ን ከዚህ በፊት በሁሉም ክልሎች የማስተዋወቅ ስራ  ሰራ መቆየቱን ገልጸው የዚህ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ዋና ዓላማ በመንግስት ግዥ አፈፃፀም ዙሪያ የሚታዩ የስነ-ምግባር ጉድለት ለማስቀረት፣ በግዥ ላይ የሚውለው ከፍተኛ የሀገሪቷ ሀብት አግባብ ባለው መልኩ በስራ ላይ እንዲውል ለማስቻል ይህ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መዘጋጀቱን ገልጾ ዛሬ አለም በደረሰበት የቴክኖሎጂ ውጤትና በሰለጠነ አለም ውስጥ አዲስ የሲስተም ቴክኖሎጂ ተቀብሎ  ተወዳዳሪ ያደርግ ሲስተም በመሆኑ ልንተገብረው ይገባል ብለዋል፡፡ 

ለንግዱ ማህበረሰብ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ሰፋ ያለ ማብራሪያ እና ገለፃ የተሰጠ ሲሆን ተሳታፊዎቹም ጥሩ ግንዛቤ ማግኘታቸውን እና የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የተነሱ ሲሆን ለተነሱትም ጥያቄዎችና አስተያየቶች ከባለስልጣኑ መልስ ተሰጥቶባቸው ስልጠናው ተጠናቋል፡፡

Share This News

Comment