Logo
News Photo

የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ለከተማ አስተዳደሩና ለዩኒቨርሲቲ ሴት አመራሮች ውሳኔ ሰጪነት እና ተግባቦት ላይ ትኩረት ያደረገ ስልጠና ሰጠ፡፡

የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም በዚሁ ስልጠና ላይ ተገኝተው የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት በማስተላለፍ በዩኒቨርሲቲ ከሚገኙ ሴት መምህራንና ተማሪዎች በተጨማሪ በአስተዳደሩ በተለያዩ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሴቶችን ለማብቃት በርካታ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልፀው ይህንም ተግባሩን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም በንግግራቸው አረጋግጠዋል፡፡  

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ክብርት ወ/ሮ ፈቲያ አደን በበኩላቸው እንደገለጹት በሃገራችን ከሚገኘው አጠቃላይ የህዝብ ብዛት ግማሽ ያህሉን ቁጥር የሚሸፍኑት ሴቶች ቢሆኑም ለዘመናት በነበሩ የተዛቡ አመለካከቶች ሳቢያ ከማህበራዊው፣ ከምጣኔ ሃብታዊው እና ከፖለቲካው ዘርፍ ተጠቃሚነት እና ተሳታፊነት ተገልለው የቆዩ መሆኑን ጠቅሰው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጫና እና ተፅእኖ ደረጃ በደረጃ እየቀነሰና ተስፋ ሰጪ የሆኑ ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆናቸውን ገልጸዋል። 

ክብርት አፈጉባዔ ወ/ሮ ፈቲያ አክለው ትርጉም ባለው መልኩ የሴቶችን ተጠቃሚነትና ተሳታፊነት ለማሳደግ ግን አሁንም ያልተቋረጠ የሁላችንም ሰፊ ርብርብ  ይጠይቃል ብለዋል፡፡ በተለይም ይህንን በሁሉም ዘርፍ አናሳ የሆነ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግና የሴቶችን ውሳኔ ሰጪነትለማጎልበት  በየጊዜው ተከታታይነት ያላቸው ስልጠናዎችን በማዘጋጀት የሴቶችን አቅም መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በስልጠናው ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኢ.ፌ.ድ.ሪ የገቢዮች ሚኒስቴር ሚንስትር ዲዔታና የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ አባል የሆኑት ክብርት ወ/ሮ መሠረት መስቀሌ እንዳሉት አመራር ሴቶች በተቀመጡበት የኃላፊነት ቦታ ስራቸውን በብቃት በመወጣት ውጤታማ መሆን እንደሚጠበቅባቸው አብራርተዋል። ምንም እንኳን ሴት አመራሮች ተደራራቢ የሆነ ኃላፊነት ያለባቸው ቢሆንም አስቸጋሪ የሆኑ ሁኔታዎችን የመቋቋም አቅማቸውን በማጠናከር ውጤታማ በመሆን ለሌሎች ሴቶች አርያ መሆን ይጠበቅባቸውዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡  

ወ/ሮ መሠረት አክለውም  የመንግስት ተቋማትን በበላይነት ለመምራት እድል ያገኘን ሴቶች ብቁ አመራር በመስጠት በስራችን ሞዴል በመሆን ሌሎች ሴቶችን በስራችን እያበቃን ለሴቶች ውሳኔ ሰጪነት መጎልበት የሚጠበቅብንን መወጣት ይኖርብናል ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

ለ3 ተከታታይ ቀን የቆየውና የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ያዘጋጀው ስልጠና  የድሬደዋ አስተዳደር እና የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ሴት አመራሮች ተካፋይ የሆኑበት ሲሆን በአመራር ውሳኔ ሰጪነት፣ በተግባቦት እና በክትትልና ግምገማ ትኩረት ያደረጉ ስልጠናዎች ተሰጥተዋል፡፡

በመጨረሻም ስልጠናቸውን ሙሉ ለሙሉ ተከታትለው ላጠናቀቁ  በተለያዩ የአመራርነት ደረጃ ላይ ለሚገኙ ተሳታፊዎች የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡

Share This News

Comment