Logo
News Photo

የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ በድሬዳዋ ለሚገኙ 7ኛ እና 8ኛ ክፍል የሳይንስና የሂሳብ መምህራን በሳ.ቴ.ም.ሂ (STEM) ዙሪያ ስልጠና ሰጠ

በድሬዳዋ አስተዳደር ስር በሚገኙ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የሳይንስ ትምህርት ዓይነቶች (ፊዚክስ፤ባዮሎጂና፤ኬሚስትሪ) እና ሂሳብ መምህራን ለሁለት ቀን የቆየ ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡


በስልጠናው መክፈቻ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ወንዲፍራው ደጀኔ እንዳሉት የድሬ ዳዋ ዩኒቨርሲቲ በሳ.ቴ.ም.ሂ (STEM) ፕሮግራም በሳይንስና በሒሳብ ትምህርት የተሻለ ውጤት ያላቸውን የ1ኛ እና የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በንድፈ-ሀሳብ የቀሰሙትን  እውቀት  በተግባር ልምምድ የሚያዳብሩበት ሁኔታ በማመቻቸት ነገ ከራሳቸው አልፈው ሀገራቸውን መጥቀም የሚችሉ ዜጎችን ለመፍጠር የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ መሆኑን አስረድተው ዛሬ የተዘጋጀው ስልጠና ከተማሪዎች ባሻገር የሳይንስና ሂሳብ መምህራንን የማስተማር ብቃት ለማሻሻልና በሳ.ቴ.ም.ሂ (STEM) ዙሪያ ያለቸውን ግንዛቤ በማሳደግ ተማሪዎቻቸውን የበለጠ እንዲረዱ ታስቦ ነው ብለዋል፡፡ 


የSTEM ማዕከል አስተባባሪ መ/ር ግዛው ገ/ስላሴ በበኩላቸው ስልጠናው በሁሉም የክፍል ደረጃ ለሚያስተምሩ የሳይንስና ሂሳብ መምህራን በተከታታይ የሚሰጥ መሆኑን አስረድተው የአስተዳደሩ ትምህርት ቢሮና የትምህርት ቤት አመራሮች ከዩኒቨርሲቲው ጋር ይበልጥ ተቀራርበው እንዲሰሩና ሁሉም ትምህርት ቤቶች በSTEM ፕሮግራም ንቁ ተሳታፊ እንዲሁኑና ክትትል እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡ 


በመጨረሻም ትምህርት ቢሮን በመወከል የተገኙት አቶ ኤርሚያስ አባስ ዩኒቨርሲቲው ትምህርት ቤቶችን ለመርዳት እያደረገ ያለውን ከፍተኛ ጥረት በትምህርት ቢሮና ትምህርት ቤቶች ስም አመስግነው ሰልጠኞች ስልጠናውን በትኩረት ተከታትለው የተማሪዎቻቸውን ውጤት እንዲያሻሽሉ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ 


ስልጠናውን የዩኒቨርሲቲው የሂሳብ፤ኬሚስትሪና ፊዚክስ ትምህርት ክፍል ባልደረባ የሆኑ አራት መምህራን የሰጡ ሲሆን በስልጠናው ላይ 118 (አንድ መቶ አስራ ስምንት) የ7ኛ እና 8ኛ ክፍል የሳይንስና የሂሳብ መምህራን ተሳትፈዋል፡፡


Share This News

Comment