Logo
News Photo

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የከተሞች ገቢ ሪፎር ፕሮጀክት ጽ/ቤት ከድሬድዋ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ከተለያዩ ክልሎች ለተውጣጡ የመሬትና ፕላን ባለሙያዎች የሙያ ደረጃ ምዘናን አስመልክቶ ስልጠና መሰጠት ተጀመረ፡፡

በስልጠናው መክፈቻ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት  በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የከተማ አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ አቶ ፋንታ ደጀን እንዳሉት የከተሞች ልማት ለሀገር ምጣኔሀብታዊ እድገት የማይተካ ሚና የሚጫወቱ መሆኑን ጠቁመው ለከተሞች ልማትና እድገት የከተማ መሬት ሃብት ዋነኛ ቁልፍ ጉዳይ በመሆኑ የመሬት አስተዳደርን በዘመነ መንገድ መምራትና ዘርፉንም በሰለጠ የሰው ኃይል ማደራጀት ያስፈልጋል፤ ይህ ደግሞ ልንደርስበት ላሰብነው የከተሞች እድገት በአጭር ጊዜ ውስጥ መድረስ ያስችለናል ብለዋል፡፡

በከተማ ልማት ዘርፍ ትልቅ ሀብት የሆነው መሬትን ዓለም በደረሰበት ቴክኖሎጂ ለማስተዳደር ብቁና እውቀት ባላቸው አመራሮችና ባለሞያዎች ከማደረጀትም ባለፈ በየጊዜው የሙያ ብቃትን ማረጋገጥ ለዘርፉ እድገት የሚኖረው ፋይዳ የጎላ ነው ያሉት ደግሞ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም ናቸው፡፡   

ዶ/ር ኡባህ አክለው ለዚህ ደግሞ በሀገር አቀፍ ደረጃ መንግስት በብዙ ከተሞቻችን የሚስተዋለውን የመልካም አስተዳደር ችግር እና ብልሹ አሰራር ከመቅረፍ አኳያ የከተማ መሬት ይዞታ ምዝገባና መረጃ  ስርዓት ከማዘመን ረገድ ሳይንሳዊ መርህን ተከትሎ መስራት ይጠበቃል ብለዋል፡፡ 

ከዚህም ጋር ተያይዞ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የዘርፉን ባለሞያዎች የእውቀትና ክህሎት ክፍተት ከመሙላት አንፃር  የሚኖራቸው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ የተጣለባቸውን ግዴታ ሊወጡ ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡ 

በዚህ ረገድም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በከተማ መሬትና ፕላን ዘርፍ በአራት የሙያ መስኮች ሰልጥነው እንዲበቁለት  እየሰራ ላለው ስራ መሳካት የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ከሰርቬይንግ ምህንድስና፣ ከአርክቴክቸር፣ ከላንድና ኢቫሉዌይሽን እና ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ትምህርት ክፍል የተመረጡ ባለሞያዎችን በማሳተፍ በስልጠናው የሚፈለገው ግብ ላይ መድረስ እንዲቻል የበኩሉን ይወጣል ሲሉ አረጋግጠዋል፡፡

በዚሁ ስልጠና ላይ የድሬደዋ አስተዳደር መሬት ልማት ቢሮ እና የሶማሌ ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ሃላፊዎች አንደተናገሩት ቅንጅታዊ አሰራርን በማጎልበት ዘርፉን ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ 

በከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የከተሞች ገቢ ሪፎርም ፕሮጀክት ጽ/ቤት ከድሬድዋ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ስልጠና ከግንቦት 29 ቀን 2014 ዓ.ም እስከ ሐምሌ 15 ቀን 2014 ዓ.ም ለ45 ቀን የሚቆይ ሲሆን በስልጠናው ላይም ከሃረሪ እና ከሶማሌ ክልል የተውጣጡ የመሬትና ፕላን ባለሙያዎች እንዲሁም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ በመሆን ከደረጃ ሁለት አንስቶ እስከ ደረጃ አምስት ያሉ የሙያ ብቃት ምዘና ስልጠናዎችን እንደሚወስዱ ከወጣው መርሀ ግብር ላይ ለማወቅ ተችሏል፡፡ 


Share This News

Comment