Logo
News Photo

በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ ሳምንት ተከበረ፡፡

በየአመቱ የሳይንስ ሳምንት በሀገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ዝግጅቶች የሚከበር ሲሆን ይህንን በአል በማስመልከት በዛሬው እለት በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት ሴሚናር ተካሂዷል።

በሴሚናሩ ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው የተፈጥሮና ኮምፒውቴሽናል ሳይንስ ኮሌጅ ዲን የሆኑት ዶ/ር ለገሰ ታደሰ ሲሆኑ በንግግራቸውም ሳይንስ ለአንድ ሃገር እድገትና ብልፅግና ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው መምህራን የሳይንስ ባህልን በማዳበር ተማሪዎች ለሳይንስ ትምህርት ያላቸውን ዝንባሌ እንዲያሳድጉ መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ 

ሴሚናሩን በንግግር የከፈቱት የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሰለሞን ዘሪሁን በበኩላቸው በመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ያሉ ተማሪዎች ለሳይንስ ትምህርት ዓይነቶች ያላቸውን አሉታዊ አመለካከት በመቀየር እና  የሳይንስ ፍቅር በውስጣቸው እንዲያድር ለማድረግ የሳይንስ ሳምንት በየአመቱ መከበሩ ሚናው የጎላ መሆኑን ገልፀዋል።

በተጨማሪም ዶ/ር ሰለሞን ዩኒቨርሲቲው በአስተዳደሩ ስር ከሚገኙ ት/ቤቶች ውስጥ በሳይንስና ቴክኖሎጂ የተሻለ እውቅትና ክህሎት ያላቸው ተማሪዎችን በመለየት የተሻለ ነገር እንዲፈጥሩ ለማስቻል የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት የሳይንስ  መምህራንን እውቀትና የማስተማር ክህሎታቸውን የሚያሻሽሉ ተከታታይ ስልጠናዎችን ዩኒቨርሲቲው የሚሰጥ መሆኑን አስታውሰው የሳይንስ ዝንባሌና የፈጠራ ችሎታ ያላቸውን ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው በተቋቋመው የሳ.ቴ.ም.ሂ (STEM) ማእከል በማስተማር ላይ እንደሚገኙም ጨምረው ተናግረዋል፡፡ 

በዚህ ሴሚናር ላይ ሁለት ፅሁፎች በዩኒቨርሲቲው መምህራን ቀርበው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን በሴሚናሩ ላይም በድሬዳዋ አስተዳደር ከሚገኙ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተጋበዙ የሳይንስ ትምህርት መምህራን እና የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ተሳትፈውበታል። 


Share This News

Comment