የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት የውስጥ የሙት ኮርት (Moot Court) ውድድር አካሄደ
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ትምህርት ቤት ከኢትዮጵያ የሕግ ትምህርት ቤቶች ማኅበር (ELSA) ጋር በመተባበር የውስጥ የሙት ኮርት (የልምምድ ችሎት) ውድድር አካሄደ። በዝግጅቱ ላይ የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዝዳንት፣ የኢትዮጵያ የሕግ ትምህርት ቤቶች ማኅበር ፕሬዝዳንት፣ መምህራን እና ተማሪዎች ተገኝተዋል።
መድረኩን የከፈቱት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር መገርሳ ካሲም ባስተላለፉት መልዕክት ብቁ እና በተግባር የታገዘ እውቀት ያላቸውን ምሩቃን ለማፍራት ዩኒቨርሲቲው በሚያደርገው ጥረት ውስጥ መሰል ውድድሮች ትልቅ ሚና አላቸው ብለዋል።
የሕግ ትምህርት ቤት ዲን አቶ ዓለምሰገደ ደጀኔ በበኩላቸው መሰል መርሃ ግብሮች የሕግ ተማሪዎችን እውቀት እና ክህሎት የሚያዳብሩ ናቸው ያሉ ሲሆን በተጨማሪም ትምህርት ቤቱ የሙት ኮርት ልምምድን በስርዓተ-ትምህርቱ እና በመማር ማስተማር ሂደቱ ውስጥ ለማካተት፣ ጠንካራ የሙት ኮርት ባህልን ለማስፈን፣ በሀገራዊ ውድድሮች ያለውን ታዋቂነት ለማስቀጠል እና ዩኒቨርሲቲው ወደ ተግባራዊ ሳይንስ ለሚያደርገው ሽግግር የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማድረግ ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
ከመክፈቻው መርሃ ግብር በኋላ በሚገባ የተዘጋጁ ቡድኖች የተሳተፉበት ውድድር ቀጥሏል። ተከራካሪ ቡድኖችን ለመዳኘት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ፣ የሰብአዊ መብት ባለሙያዎችን፣ የአካዳሚክ እና በሕግ ሙያ ላይ የተሰማሩ ከፍተኛ እውቅና እና የረዥም ጊዜ ልምድ ያላቸው ዳኞች ተሳትፎ አድርገዋል፡፡
Share This News