Logo
News Photo

ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ 5ኛውን የብዝሃነት መድረክ በድምቀት አካሄደ

የብዝሃነትና የመቻቻል ተምሳሌት በሆነችው ድሬዳዋ ከተማ የሚገኘው ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ "ብዝሃነት እና የሽግግር ፍትህ ለሀገር ግንባታ እና ዘላቂ ሰላም" በሚል መሪ ቃል ለ5ኛ ጊዜ በድምቀት አካሂዷል። ዩኒቨርሲቲው ብዝሃነትን የተቋሙ መገለጫና እሴት በማድረግ የሚሰራቸውን ስራዎች አጠናክሮ ቀጥሏል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም በመድረኩ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ድሬዳዋ በተፈጥሮዋ የታሪክ፣ የባህል፣ የቋንቋ እና የእምነቶች መገናኛ መሆኗን ገልጸዋል። ፕሬዝዳንቷ አክለውም "ዩኒቨርሲቲያችን ከአባቶቻችን የወረስነውን የመቻቻል እሴት ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍና አካባቢያዊ ፀጋዎቻችንን ለማጎልበት በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል" ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው ከውይይት ባለፈ የድሬዳዋንና የአካባቢውን ቅርሶች ለዓለም ለማስተዋወቅ በሳይንሳዊ መንገድ እየሰራ መሆኑ የገለፁት ዶ/ር ኡባሀ የአካባቢው ማሀበረሰብ ቅርሶች በ UNESCO የዓለም ቅርስነት እንዲመዘገቡ ባለሙያዎችን መድቦ ጥናት እያከናወነ ይገኛል ብለዋል፡፡


የምርምር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ተማም አወል በበኩላቸው፣ ብዝሃነት ለኢትዮጵያ የችግር ምንጭ ሳይሆን የጥንካሬና የውበት መሠረት መሆኑን አፅንኦት ሰጥተዋል። መቻቻል ለሰላም፣ ሰላም ደግሞ ለልማትና ለዕድገት ወሳኝ መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ተማም፣ አካታችነትን ለመፍጠር መደማመጥና ውይይት ቀዳሚ ተግባራት መሆን እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።


በመድረኩ ላይ ከተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመጡ ምሁራን ጥናታዊ ጽሁፎችን አቅርበው ሰፊ ውይይት ተካሂዶባቸዋል። በዝግጅቱ ላይ የተቋማት አመራሮችና የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችና ተመራማሪዎች እና የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላት ተሳትፈዋል።

Share This News

Comment