ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ‘’ከሱስ ነፃ የሆነ ትውልድ ለመፍጠር እየሰራው ነው’’ አለ
በመልካም ስነ-ምግባር የታነፀና ከሱስ ነፃ የሆነ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለመፍጠር በትኩረት እየሰራ መሆኑን የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ገለጸ። የዩኒቨርሲቲው ማርኬቲንግ ትምህርት ክፍል ለ8ኛ ጊዜ ባካሄደው የማህበረሰብ ንቅናቄ መድረክ ወጣቶችን ከአደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚነት ለመከላከል ታሳቢ ያደረገ እና በርካታ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ደማቅ መድረክ አዘጋጅቷል፡፡
በዚሁ መድረክ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ኡባህ አደም እንደገለጹት፤ ተማሪዎችን ለተለያዩ ሱሶች ሊያጋልጡ የሚችሉ በርካታ ፈተናዎች ባሉበት በዚህ ወቅት፣ የመከላከል ስራው ለድርድር የማይቀርብ የዩኒቨርሲቲው ቀዳሚ ተግባር ነው። ፕሬዚዳንቷ አክለውም፣ በመልካም ስነ-ምግባር የታነፀ ትውልድ ማፍራት የተቋሙ ዋነኛ ተልዕኮ መሆኑን ጠቁመው፣ ይህንን ግብ ለማሳካትም ዩኒቨርሲቲው በተደራጀ መልኩ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀው መድረኩን ላዘጋጁት አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በዕለቱ የአደንዛዥ እፅን በተመለከተ ገለፃ እና ስልጠና የሰጡት የአእምሮ ሕክምና ትምህርት ክፍል መምህር ጄኔኑስ ታደሠ በበኩላቸው፤ ወጣቶች ዛሬ ላይ የሚያደርጓቸው ምርጫዎች ለነገው ሕይወታቸው መሠረት መሆናቸውን አስገንዝበዋል። ተማሪዎችም ሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች ለነገ ህልውናቸው ሲሉ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው እራሳቸው ከሱስ ሊያርቁ እንደሚገባም አሳስበዋል።
ይህ የንቅናቄ መድረክ በተማሪዎች ዘንድ ያለውን ግንዛቤ ከማሳደጉ ባለፈ፣ ዩኒቨርሲቲው ለተማሪዎቹ ሁለንተናዊ ብቃትና ስነ-ልቦናዊ ጥንካሬ የሰጠውን ትኩረት የሚያሳይ መሆኑ በመድረኩ ተገልጿል።
Share This News