Logo
News Photo

ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የ2015 ዓ.ም ሁለተኛውን ዙር የተጠናቀቁ የምርምር ስራዎች የግምገማ አከናወነ፡፡

በግምገማ መድረኩ መክፈቻ ላይ በመገኘት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሰለሞን ዘሪሁን ሲሆኑ በንግግራቸውም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዩኒቨርሲቲው እየተደረጉ ያሉት የምርምር ስራዎች ከብዛትም ሆነ ከጥራት  አንጻር  በከፍተኛ መጠን ማሳደግ የተቻለበት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ 


እንደ ዶ/ር ሰለሞን ገለፃ የዩኒቨርሲቲው የምርምር ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት የአሰራር ስርአቱን  ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ እያዘመነ በመምጣቱና ለምርምር ስራ የሚዉል ሶፍትዌር አሰርቶ የምርምር ስራዎች ሙሉ በሙሉ ወረቀት አልባ በማድረጉ ምክንያት ተመራማሪዎች እና ገምገሚዎች የጥናትና ምርምር ስራቸዉን ወደ ምርምር ጉዳዮች ቢሮ ሳይመጡ ባሉበት ቢሯቸዉ ሆነው ማንኛውንም የምርምሩን ሂደት  የሚከዉኑበት እድል በመፍጠር የወረቀት፣ የፕሪንተርና ማባዣ ቀለም እና የሰዉ ሀይል ብክነትን እንዲቀንስ አድርጓል፡፡ ዩኒቨርሲቲው የያዘውን ርዕይ ማሳካት እንድንችል በተለይ በጥናትና ምርምሩ ዘርፍ  የዩኒቨርሲቲው መምህራንና ተመራማሪዎች ወቅቱን ያገናዘበ ስራዎችን በመስራት የበኩላቸው ድርሻ ይወጡ ዘንድ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡ በመቀጠልም ተመራማሪዎችም ይሁኑ ገምጋሚዎች የተሰራዉን ሶፍትዌር በደንብ እንዲጠቀሙ አስገንዝበዋል፡፡ በመጨረሻም የተጠናቀቁትን ምርምሮች በዩኒቨርሲቲዉ ጆርናል ላይ እንዲያሳትሙ ጥሪ አቅረበዋል፡፡ 


በዚሁ የግምገማ መድረክ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር መገርሳ ቃሲም በበኩላቸው በምርምር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ላይ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ላይ ያሉ ከዚህ በፊት ሲያስቸግሩ የነበሩትን ማነቆዎች በመፈታቱ መምህራኖቻችን ዛሬ ለምናየዉ ዉጤቶች በቅተናል፡፡ የምርምር ሥራዎች  ወደመሬት ወርደው የአካዳሚክ ስራዎችንና የማኅበረሰቡን ችግር መፍታት እንዲችሉ ተመራማሪዎች ጥረታቸውን እስከ ጥግ ድረስ ማደረስ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡ 


በዚህ ለሁለት ቀን በቆየውና የዩኒቨርሲቲው የምርምር ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ባዘጋጀው የምርምር ሥራዎች የግምገማ መድረክ ላይ ቁጥራቸው ከ42 በላይ የሆኑ ያለቁ የምርምር ስራዎች ቀርበው አስፈላጊው ግምገማና ውይይት የተደረገባቸው መሆኑን በድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት ረ/ፕሮፌሰር ይታገሱ ስንታየሁ ተናግረዋል።  


በመጨረሻም ረ/ፕሮፌሰር ይታገሱ እንደተናገሩት በቀጣዮቹ ጊዜያት አሁን የጀመረዉን ወረቀት አልባ ስራችን በማጠናከር አላስፈላጊ እንግልትንና ወጪዎችን በመቀነስ በዩኒቨርሲቲው መምህራን ዘንድ በምርምር ዙርያ ያለዉን መነቃቃት ይበልጥ በማስቀጠል ችግር ፈቺ የሆኑ የምርምር ውጤቶችን  ለአካዳሚኩ እና ለአካባቢዉ ማኅበረሰብ የሚደርስበትን መንገድ ዳይሬክቶሬቱ እንደሚያመቻች ቃል ገብተዋል፡፡ 


Share This News

Comment