Logo
News Photo

በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የማስተማሪያና የሪፈራል ሆስፒታል የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራዎች ማስጀመሪያ መርሀ-ግብር ተካሄደ፡፡

የ2016 በጀት ዓመት የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ሁሉንም ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮግራም በዩኒቨርሲቲው የማስተማሪያና የሪፈራል ሆስፒታል ቅጥር ግቢ ውስጥ የዕለቱ የክብር እንግዳ ክቡር አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ በተገኙበት የማስጀመሪያ መርሀ-ግብሩ ተካሄዷል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት ዋና ተጠሪ ክቡር አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ በዚሁ መርሀ-ግብር ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን በንግግራቸው በአስተዳደሩ የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ቀደም ባሉ ጊዜያት ተጀምሮ መልካም ተሞክሮ የተገኘበት መሆኑን ጠቅሰው የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በማድረግ የህዝባችን ፍላጎት ለማሟላት ዓላማውን በመደገፍ ይበልጥ መሰራት እንደሚኖርበት ጠቅሰዎል።

በዚህ የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሀ-ግብር ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም እንደገለፁት አጋጣሚው ዩኒቨርሲቲው ወደ ህብረተሰቡ ቀርቦ ሁሉን ተጠቃሚ የሚያደርጉ እና ከዩኒቨርሲቲው ጋር የሚያስተሳስሩ የአገልግሎት ስራዎችን ዩኒቨርሲቲው መስጠቱ እጅግ እንዳስደሰታቸው ገልጸው በዚህ የበጎ ስራ ላይ የጤና ባለሙያዎቻችን በስፋት እንደሚሳተፉበት እና ስራው በተሳካ መንገድ እንዲያከናውኑ ጥሪያቸውን አቅርበው መርሀ-ግብሩን በይፋ መጀመሩን አብስረዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ለምለም በዛብህ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሀገራዊ ተልዕኮና ማስፈፀሚያ አቅጣጫ ላይ በተመለከተ መልዕክታቸውን ያስተላለፉ ሲሆን የክረምት በጎ ፍቃድ ማስፈጸሚያ መርሀ-ግብሩ ለአንድ ወር የሚቆይ መሆኑን አንስተው በተለይ በዚህ አግልግሎት ላይ የጤና ባለሙያዎች የማይተካ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

ዶ/ር ሁሴን መሀመድ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ባደረጉት የእንኳን ደህና መጣሁች መልዕክትና በአንድ ወር ውስጥ ሊሰሩ የታቀዱ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራዎችን ገለፃ ያደረጉ ሲሆን የክረምት በጎ ፍቃድ ስራው ለ5,000 (አምስት ሺ ) ሰዎችን ነፃ የህክምና አገልግሎት እንደሚያገኙ ገልጸው፤ የደም ልገሳ ፕሮግራም፣ የአቅመ-ደካማ ቤቶችን ማደስ፣ ለአሰገደች የአረጋውያን መጦርያ ማዕከል የተለያዩ ድጋፎችን ማድረግ፣ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሀ-ግብር ማከናወን፣ የወገን ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረግ እና በዩኒቨርሲቲው 104.5 ኤፍ.ኤም በማህበረሰብ ሬድዮና በአካል ማህበረሰብ ወስጥ በመውረድ የጤና ነክ ትምህርቶችን ለማስተማር ዝግጅቶችን እንዳጠናቀቁ ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ፕሮግራምና የደም ልገሳ መርሃ-ግብር ተካሄዷል።

Share This News

Comment