Logo
News Photo

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲው 3ኛውን ዙር የኢንዱስትሪ ፎረም አካሄደ

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ከተለያዩ አምራች እና አገልግሎት ሰጪ ኢንዱስትሪዎች ጋር የሚያደርገውን አመታዊ የምክክር መድረክ አካሂዷል፡፡ በምክክር መድረኩ የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስር መመሪያ ፣ የተማሪ ኢንተርንሺፕ ዙሪያ የተዘጋጀ የደሰሳ ጥናት እና የድሬዳዋ ከተማ እና ኢንዱስትሪዎች ትስስር ታሪካዊ ዳራ፣ ነባራዊ ሁኔታ እንዲሁም መፃኢ እድሎችን በተመለከተ የተዘጋጁ ሰነዶች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡  

በመድረኩ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም ‘’ዩኒቨርሲቲው ከኢንዱስትሪዎች ጋር ተቀራርቦ ለመስራት፣ የኢንዱስትሪዎች ያሉባቸውን ችግሮች ጥናትን መሰረት ባደረገ መልኩ መፍትሔ ለመስጠት እንዲሁም የኢንዱስትሪ ባለሙያዎችን በመማር ማስተማር ሂደት ውስጥ ተሳታፊ በማድረግ ተማሪዎች የኢንዱስትሪ ልምድ እንዲያገኙ እንዲሁም ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ አበክሮ ይሰራል’’ ብለዋል፡፡ 

ከኢንዱስትሪዎች ጋር የሚደረገውን ውይይት መነሻ በማድረግ የፓሊሲ ሰነድ ሊዘጋጅ ይገባል ያሉት ዶር ኡባህ በየአመቱ የሚደረገው ይህ ፎረም ቀጣይነት እንዲኖረው ኢንዱስትሪዎችን ባሳተፈ መልኩ እና ተሞክሮዎችን በየጊዜው እየቀመሩ ቀጣይነት ያለው እና ስኬታማ የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስር ይፈጠር ዘንድ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት እንደሚኖርበት ጠቁመዋል፡፡

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ምርምር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ዶር ተማም አወል በበኩላቸው የዩኒቨርሲቲ እና ኢንዱስትሪ ትስስር በመማር ማስተማር ስራዎች ላይ ከሚደረግ ስራ በተጨማሪ ችግር ፈቺ ምርምሮችን በጋራ የመስራት፣ ምሁራንን በመጠቀም የማማከር አገልግሎት የመስጠት እንዲሁም የቴክኖሎጂ ሽግግረ ስራዎችን መስራት የሚያስችል ሰፊ እድሎችም ያሉት መሆኑን አመላክተዋል፡፡

Share This News

Comment