Logo
News Photo

ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል በትምህርት ፖሊሲ ላይ ያተኮረ የክርክር መድረክ አዘጋጀ

በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ የሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያላቸውን የትምህርት ፖሊሲ አማራጮች ለህዝብ የሚያስተዋውቁበትና እርስ በእርስ የሚከራከሩበት መድረክ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ተካሄደ።

መድረኩን የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል ያዘጋጀው ሲሆን፣ ዓላማውም ፓርቲዎች ለሀገሪቱ የትምህርት ሥርዓት ያላቸውን ራዕይ መራጩ ማህበረሰብ በዝርዝር እንዲረዳው ማስቻል ነው። በመድረኩ ላይ ገዥውን የብልፅግና ፓርቲን ጨምሮ 6 ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተገኝተው የትምህርት ፖሊሲዎቻቸውን አቅርበዋል።

ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ እድገት፣ ማህበራዊ ፍትህ እና ኢኮኖሚያዊ ብልጽግና የትምህርት ሥርዓት የሚጫወተው ሚና የማይተካ መሆኑ በመድረኩ ላይ ተመላክቷል። የፓርቲዎቹ ፖሊሲዎች ከቅድመ መደበኛ ትምህርት ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ድረስ የሚዘልቁ መሰረታዊ አጀንዳዎችን የያዙ እንዲሆኑና በጥልቀት ሊመረመሩ እንደሚገባም ተገልጿል።

ፓርቲዎቹ ካነሷቸው የመከራከሪያ ነጥቦች መካከል የተማሪዎችን ምገባ፣ የዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝነት በተመለከተ፣ የመምህራንን ጥቅማ ጥቅም፣ የመማሪያ ቋንቋ፣ ትምህርት ጥራት፣ የተማሪዎች ምዘና እና ፈተና፣ የጎልማሳ ትምህርት ተደራሽነት፣ የአካል ጉደተኞች ትምህርት እና ክትትል እንዲሁም የትምህርት ስርዓት ማሻሻያ በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ አቋማቸውን አንፀባርቀዋል።


መድረኩ ማህበረሰብ በስሜት ሳይሆን በእውቀትና በፖሊሲ አማራጮች ላይ ተመስርቶ ውሳኔ እንዲሰጥ ይረዳል ተብሏል። በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው እንደ አንድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ላይ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ የሚያስችለው መሆኑ ተጠቁሟል።

Share This News

Comment