Logo
News Photo

"ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነዳጅ አምራች ሀገራትን እንደ አማራጭ ልትጠቀም ይገባል" ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉ

ኢትዮጵያ በነዳጅ አቅርቦት ረገድ ያላትን ተጋላጭነት ለመቀነስ ነዳጅ አምራች የሆኑ የአፍሪካ ሀገራትን እንደ ዋነኛ አማራጭ ልትጠቀም እንደሚገባ አንጋፋው ዲፕሎማትና ምሁር ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉ አሳሰቡ።

ባለፉት 40 ዓመታት ኢትዮጵያን በአምባሳደርነት፣ በከፍተኛ የመንግስት አማካሪነት እና በዩኒቨርሲቲ መምህርነት ያገለገሉት የፓለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁሩ ፕሮፌሰር ብሩክ፤ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ተገኝተው በወቅታዊ ቀጠናዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ፕሮፌሰሩ በመካከለኛው ምስራቅ እየተከሰተ ያለውን የፖለቲካ ትኩሳት፣ ጦርነት እና የሆርሙዝ ሰርጥ የመዘጋት ስጋት በዝርዝር ዳስሰዋል። በተለይም በኢራን እና በአሜሪካ መካከል ያለው ፍጥጫ ሊያስከትል የሚችለውን የጂኦ-ፖለቲካዊ እና የኢኮኖሚ ለውጥ ዓለም በንቃት ሊጠብቀው እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የሆርሙዝ ሰርጥ መዘጋት በዓለም የነዳጅ ንግድ ላይ የሚፈጥረውን ጫና በቁጥራዊ መረጃዎች ያስረዱት ፕሮፌሰሩ፤ ይህም ሁኔታ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራትን ኢኮኖሚ በእጅጉ እንደሚፈትን አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ በዚህ ወቅት ልትከተለው ስለሚገባው ዲፕሎማሲያዊ አቅጣጫ ፕሮፌሰር ብሩክ የሚከተሉትን ነጥቦች አፅንዖት ሰጥተውባቸዋል፦

ጥንቃቄ የተሞላበት ክትትል፦ ወቅታዊውን ዓለም አቀፍ ትኩሳት ከሀገራዊ ጥቅም አንጻር በጥንቃቄ መከታተል።

ከጎራተኝነት መራቅ፦ ከየትኛውም ተጻራሪ ኃይሎች ጎራ አለመሰለፍ

ብሔራዊ ጥቅም ማስቀደም፦ የውጭ ፖሊሲው ማጠንጠኛ የሀገርን የረጅም ጊዜ ጥቅም ማስጠበቅ አትኩሮ መስራት

የሆርሙዝ ሰርጥ ስጋትን ለመቋቋም "አፍሪካዊ መፍትሄ" ያቀረቡት ፕሮፌሰሩ፤ የአፍሪካ ነዳጅ አምራች ሀገራት ምርታቸውን ለአህጉሪቱ ሀገራት ቅድሚያ ሰጥተው የሚያቀርቡበት ሥርዓት ሊዘረጋ እንደሚገባ ገልጸዋል። ኢትዮጵያም ከባህረ ሰላጤው ሀገራት ባለፈ፣ የአፍሪካ ሀገራትን እንደ አማራጭ የነዳጅ ምንጭ ማጤን እንደሚገባ መክረዋል።

Share This News

Comment