የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ እና የሶማሌ ክልል ክህሎት እና ስራ ፈጠራ ቢሮ በስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ ለመስራት ተስማሙ
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶችን ለመፍታትና የስራ ዕድል ፈጠራን ለማነቃቃት ካለው ራዕይ በመነሳት፣ ከሶማሌ ክልል ክህሎት እና ስራ ፈጠራ ቢሮ ጋር በትብብር ለመስራት ተስማምቷል። ስምምነቱ በዋናነት በሶማሌ ክልል የሚገኙ ወጣቶች የክህሎት ባለቤት ማድረግ፣ ወጣቶች በስራው አለም ተወዳዳሪና ስራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ማስቻል እንዲሁመ ዩኒቨርሲቲው የሚያበለፅጋቸውን ቴክኖሎጂዎችን ለክልሉ ስራ ፈጣሪዎች ተደራሽ ለማድገረግ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም በፊርማ ስነ-ሥርዓቱ ላይ በመገኘት ባስተላለፉት መልዕክት "ዩኒቨርሲቲው የማህበረሰቡን ችግሮች የሚቀርፉ፣ ለወጣቶች የስራ እድል የሚፈጥሩ እንዲሁም የተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ የሚያዘምኑ ቴክኖሎጂዎችን በማበርከት ላይ ይገኛል" ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በተለይ ለወጣቶች የስራ እድል የሚፈጥሩ በርካታ ማሽኖችን አምርቶ የባለድርሻ አካላትን በትብብር የመስራት ተነሳሽነትን እየተጠባበቀ መሆኑን ጠቁመው "ዛሬ ከሶማሌ ክልል ክህሎት እና ስራ ፈጠራ ቢሮ ጋር የተደረሰው ስምምነት ዩኒቨርሲቲው ስራን ከመፍጠር አንፃር ትርጉም ያለው ተፅዕኖ መፍጠር የሚችሉ ቴክኖሎጂዎችን ለህብረተሰቡ በተለይ ለወጣቱ እንዲያደርስ ያግዘዋል" ብለዋል፡፡
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ምርምር እና ቴከኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ተማም አወል በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ስራ አጥ ወጣቶችን ማዕከል ያደረጉ በርካታ አጫጭር ስልጠናዎችን ሲሰጥ መቆየቱን አስታውሰው በቀጣይነትም የወጣቱን የስራ ክህሎት የሚያጎለብቱ፣ የቴክኖሎጂ ፍላጎት የሚያሟሉ እንዲሁም ዘመናዊ አሰራርን የሚያሰርፁ ስልጠና እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ስራዎች ከሶማሌ ክልል ክህሎት እና ስራ ፈጠራ ቢሮ ጋር እንደሚሰሩ ጠቁመዋል፡፡
ሁለቱም ተቋማት የመንግሥትን የልማት ፖሊሲዎችና ስልታዊ ዕቅዶች መሠረት በማድረግ፣ ዘላቂነት ያላቸውን ፕሮግራሞች በመቅረጽ፣ የተቋማዊ አቅም ግንባታ ሥራዎችን በማጠናከር እንዲሁም የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን በጋራ ለማሻሻል እንደሚሰሩ ተጠቁሟል። አጋርነቱ በተለይም በምርምርና ልማት (R&D) ዙሪያ የተቀናጀ ጥረት ለማድረግና የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ውጤቶችን ወደ ማኅበረሰቡ ዘልቀው እንዲገቡ በማሸጋገር ረገድ ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል። በተጨማሪም ስምምነቱ የአካዳሚክ ባለሙያዎችንና የመምህራንን የዕውቀት አድማስ የሚያሰፉ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን፣ የጥራት ማረጋገጫ ሥራዎችን እና የጋራ የሥልጠና መድረኮችን በስፋት ለማዘጋጀት ትኩረት ሰጥቶ ይሠራል።
ለሦስት ዓመታት ጸንቶ የሚቆየው ይህ ስምምነት፣ ለአካባቢው ማኅበረሰብ የሚሰጡ የክህሎት ልማትና የሥራ ዕድል ፈጠራ አገልግሎቶችን በማሻሻልና በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ተብሎ ይጠበቃል።
Share This News