ዩኒቨርሲቲው ከድሬዳዋ አስተዳደር ንግድ፣ ኢንደስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ጋር በትብብር የሚሰራው"የገጠር ኢንዱስትሪያላይዜሽን እምቅ አቅም ልየታና ግምገማ " የተሰኘውን ፕሮጀክት ማስጀመሪያ ፕሮግራም ተካሄደ።
በአስተዳደሩ የገጠር ክላስተሮች የሚገኙ እምቅ አቅሞችን የመለየት እንዲሁም አካባቢያዊ ፀጋዎች ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለልማት የሚውሉበትን መንገድ የሚያመላክት ፕሮጀክት ዛሬ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች እና የአስተዳደሩ ንግድ፣ ኢንደስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ አመራሮች በተገኙበት በይፋ ተጀምሯል፡፡
በፕሮግራሙ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ኡባህ ‘’አደም እንደ ከተሞቻችን ሁሉ የገጠር ማኅበረሰባችንም ለውጥና እድገትን ይሻሉ’’ ያሉ ሲሆን ‘’የድሬዳዋ አስተዳደር ሰፊ የገጠር ቀበሌዎችን የያዘ አስተዳደር እንደመሆኑ ሰፊ እና እምቅ አቅም ያለው አካባቢ ነው’’ ብለዋል፡፡ ይህንን አቅም መለየት መገምገምና አቅምን ደምሮ የተሻለ የኢኮኖሚ ሰንሰለት በመፍጠር የገጠሩን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ ማድረግና የእድገት ተዋናይ እንዲሆኑ ማስቻል የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሊሆን ይገባል ያሉት ዶ/ር ኡባህ ‘’የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በአስተዳደሩ ገጠር ወረዳዎች በሚሰሩ የልማት፣ የምርምር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎች ላይ በስፋት ይሰራል’’ ብለዋል፡፡
የዩኒቨርስቲው የምርምርና ቴክኖሎጅ ሽግግር ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ተማም አወል በበኩላቸው ‘’ፕሮጀክቱ ከዚህ ቀደም የተጠናቀቁና አሁን በመጠናቀቅ ላይ ካሉት ተከታታይነት ያላቸው ፕሮጀክቶች የቀጠለና የገጠሩን ማኅበረሰብ በሀገር ደረጃ የተጀመሩ በርካታ የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ልማት ስራዎች ተሳታፊ የምናደርግበት ትልቁ ፕሮጀክታችን ነው’’ ሲሉ ተናግረዋል።
Share This News