የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ያሉባቸውን ተግዳሮቶች ታሳቢ ያደረገ የስልጠና ማዕከል ለማቋቋም መከሩ
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የተለያዩ የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን ያሳተፈ እና ፋብሪካዎች ባሉባቸው ተግዳሮቶች ዙሪያ የሰራውን ጥናት ይፋ ያደረገበት መርሃ ግብር ዛሬ ተካሄደ፡፡ ድሬዳዋ ሲሚንቶን በማምረት ቀዳሚ ከተማ ከመሆኗም በላይ 3 የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የሚገኙባት ለዘርፉ እጅግ ተፈላጊ የሆኑ ጥሬ እቃዎች የሚገኙባት ከተማ ናት፡፡
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ይህንኑ አካባቢያዊ ፀጋ ከመጠቀም አንፃር የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን መለየት የሚያስችል ጥናት በማካሄድ ከመላው ኢትዮጲያ የተውጣጡ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች ባሳተፈ መርሃ ግብር ይፋ አድርጓል፡፡ ጥናቱ በሲሚንት ኢንዱስትሪ የሚስተዋለውን ብቁ የሰራተኛ እጥረት መቅረፍ የሚያስችል የስልጠና ማዕከል እንዲቋቋም ምክረ ሃሳብ አቅርቧል፡፡
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም እንደገለጹት፤ ዩኒቨርሲቲው የከተማዋንና የአካባቢውን ኢንዱስትሪያዊ ዕድገት ለመደገፍ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል። ዶ/ር ኡባህ አክለውም በሲሚንቶ ኢንዱስትሪው ውስጥ የሚስተዋለውን የቴክኒክና የክህሎት ክፍተት ለመሙላት ቁልፍ ሚና የሚኖረው የስልጠና ማዕከል በማቋቋም ኢንዱስትሪዎችን ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የቡዛየሁ ታደለ እና ቤተሰቡ ፋውንዴሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ብርሃኑ ደግፍ በበኩላቸው የሲሚንቶውን ዘርፍ በጥናት እና እውቀት መምራት ለዘርፉ እድገት ከሚኖረው ከፍተኛ ፋይዳ በላይ በፋብሪካዎቹ እና ዩኒቨርሲቲዎች መካከል ያለውን የስራ ግንኙነት ለማጠናከር ይረዳል ብለዋል፡፡
Share This News