Logo
News Photo

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች፣ መምህራን እና የአስተዳደር ሠራተኞች በዩኒቨርሲቲው የ2015 በጀት ዓመት አፈፃፀምና በ2016 በጀት ዓመት እቅድ ላይ ተወያዩ፡፡

በዩኒቨርሲቲው የእቅድ ዝግጅት፣ ክትትልና ግምገማ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት ረ/ፕ ላመስግን አየለ በዩኒቨርሲቲው ባሳለፍነው የ2015 በጀት ዓመት በመማር ማስተማር፣ በጥናትና ምርምር፣ በማኅበረሰብ አገልግልት እንዲሁም በፕሮጀክቶች ግንባታና በመሠረተ ልማት ዝርጋታ የተሠሩ ሥራዎችን በዝርዝር በማቅረብ አብራርተዋል፡፡

በዚህ መሠረትም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በመማር ማስተማር ተልዕኮው በአገር አቀፍ ደረጃ በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ተመራቂ ተማሪዎች እንዲወስዱ የተደረገውን የመወጫ ፈተና አስመልክቶ በስኬት ማጠናቀቅ እንዲቻል ከዝግጅት፣ ከትግበራ እና ከመሠረተ ልማት ዝርጋታና ግንባታ ጋር ተያይዞ የተሠሩ ሥራዎች ውጤታማ ነበሩ፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በዩኒቨርሲቲው በጥናትና ምርምሩ መስክም ባሳለፍነው የ2015 በጀት ዓመት 81 የተጠናቀቁ የምርምር ሥራዎች የቀረቡበት እና 51 የምርምር ሥራዎችን ደግሞ በታወቂ ጆርናሎች ማሳተም የተቻለበት ዓመት ነበር፡፡

ዩኒቨርሲቲው በማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎቱም በድሬዳዋ አስተዳዳር አቅመ ዳካማ እና ተጋላጭ የምህበረሰብ ክፍሎችን  ትኩረት ያደረጉ ሥራዎች የሰራ ሲሆን ከእነዚህም መካከል የአቅመ ደካማ ወገኖች ቤት ግንባታና እድሳት፣ ቤተሰቦቻቸው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ህፃናት ተማሪዎች የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ ድጋፍ፣ የትምህርት ቤት እድሳት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ 

ሌላው በድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ባላፈው 2015 በጀት ዓመት ከተሰሩ ሥራዎች መካከል ዩኒቨርሲቲውን የተመለከቱ አጠቃላይ መረጃዎች በአንድ ላይ ወደ HEMIS የመረጃ ቋት ውስጥ ለማስገባት የተሰራው ሥራ ተጠቃሽ መሆኑን ባቀረቡት ሪፖርት ላይ ያመለከቱት ረ/ፕ ላመስግን ይህ ደግሞ ከዚህ ቀደም ከመረጃ አያያዝ ጋር በዩኒቨርሲቲው ይተዩ የነበሩ ክፍተቶችን የሚደፍኑ ናቸው ብለዋል፡፡

እንዲሁም ዩኒቨርሲቲው በበጀት ዓመቱ አራት ቴክኖሎጂዎች በዩኒቨርሲቲው መምህራን በልጽገው ከኢ.ፌዴሪ አዕምራዊ ንብርት ባለስልጣን የፈጠራ የባለቤትነት መብት ማግኘት የቻሉበት ሥራም ተጣቃሽ ነው፡፡ 

ከዚህ በተጨማሪ በበጀት ዓመቱ ከዚህ ቀደም በዩኒቨርሲቲው ጎልቶ ይታይ የነበረውን የውሀ አቅርቦት ችግርን ለመቅረፍ በተሠራው ሥራ ሁለት ጥልቅ ጉድጓዶችን በማስቆፈርና የመስመር ዝርጋታን በማጣናቀቅ አገልግልት እንዲጀምር መደረጉም ተጣቃሽ ነው ብለዋል፡፡ 

የዩኒቨርሲቲውን የውስጥ ገቢ ለማሳደግ ከተሰሩ ስራዎች አንዱ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ጠቅላላ ንግድ እና ማማከር ኢንተርፕራይዝ ተቋቁሞ ስራ መጀመሩ ነው፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የዩኒቨርሲቲው የ2016 በጀት ዓመት እቀድ በዝርዝር ቀርቦም ማብራሪያ ተሰጥቶበታል፡፡ ይህንን ተከትሎም 

የቀረበውን የ2015 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀም ሪፖርትና የ2016 በጀት ዓመት እቅድን አስምልክቶ ከስብሰባው ተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄና አስተያቶች ቀርበዋል፡፡

በወቅቱ ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከልም የግቢ ምድረ ውበት በማሳመር በኩል ክፍተቶች አሉ ፣ የሠራተኛ ጥቅማጥቅም እና የኑሮ ውድነቱን ከማቃላል እንፃር ምን ታስቧል ..? የሚሉና መሰል ጥያቄና አስተያየቶች ቀርበው የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተውበታል፡፡

እንደ ዶ/ር ኡባህ ገለፃ ከሆነ በአዲሱ በጀት ዓመት ዩኒቨርሲቲውን ለተማሪዎች ፣ለመምህራንና ለአስተዳደር ሠራተኞች ምቹ የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ፡፡ በአሁኑ ሰዓት በተለይ የመንግስት ሠራተኛውን በእጅጉ እየፈተነ የሚገኘውን የኑሮ ውድነት በተቻለ አቅም ለመቀነስ ዩኒቨርሲቲው በቅርቡ ህጋዊ እውቅና እንዲያገኝ ባደረገው ኢንተርፕራይዙ በኩል የተለያዩ ተግባራትን ያከናውናል ፡፡ መምህራኑና ሠራተኛው በሸማች ማህበር ተደራጅቶ የሚንቀሳቀስ ከሆነ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግም ዩኒቨርሲቲው ዝግጁ መሆኑን ዶ/ር ኡባህ በዚህ ወቅት አረጋግጠዋል፡፡

በመጨራሻም ዩኒቨርሲቲው በአዲሱ በጀት ዓመት የሰነቀውን ርዕይ ከማሳካት አንፃር በተለይም ደግም ወደ አፕላይድ ዩኒቨርሲቲነት የሚያደርገው ሽግግር ሙሉ ለሙሉ ስኬታማ ማድረግ እንዲችል የመላው የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ርብርብር ወሳኝ ነው ያሉት ዶ/ር ኡባህ  ሁላችንም በየተሠማራንብት የሥራ መስክ ውጤታማ በመሆን  የበኩላችን እንወጣ በማለት ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡


Share This News

Comment