Logo
News Photo

የቀለአ'ድ ማህበረሰብ-አቀፍ የዱር እንሰሳት ጥብቅ ሥፍራን በተመለከተ ከባለድርሻ አካላትና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ውይይት ተደረገ፡፡

ላለፉት ሁለት ዓመታት የቀለአ'ድ ማህበረሰብ አቀፍ የዱር እንሰሳት ጥብቅ ሥፍራ ለመከለል በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ፤ ድሬዳዋ ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት፤ እንዲሁም በኢትዮጵያ የዱር እንሰሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ትብብር ሲሰሩ የነበሩ ስራዎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የውይይት መድረክ ተካሄደ።


በዚህ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ከድሬዳዋ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት ኃላፊ ተወካይ ወ/ሮ ነኢማ ኢብራሂም ሲሆኑ በንግግራቸውም ጥብቅ ስፍራው ለዚህ ይደርስ ዘንድ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። 


የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ፅ/ቤት ሃላፊ አቶ ገበየሁ ጥላሁን በበኩላቸው ቀለአ'ድ ለወደፊቷ ድሬዳዋ አዲስ ተስፋ መሆኑን በመግለፅ አስተዳደሩ የማኅበረሰብ አቀፍ ጥብቅ ሥፍራው እውን እንዲሆን የሕግ ማዕቀፉን ከማፅደቅ ጀምሮ አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።


የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የሪሰርችና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ፕሬዝዳንትን ወክለው መልዕክት ያስተላለፉት የዩኒቨርሲቲው የምርምር ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ደይሬክተር ረ/ፕሮፌሰር ይታገሱ ስንታየሁ በበኩላቸው የቀለአ'ድ ጥብቅ ስፍራ እውን እንዲሆን ቀጣይ ሥራዎች ላይ ሁሉም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን እንዲወጡ አሳስበው በዚህ ረገድ ዩኒቨርሲቲው የሚጠበቅበትን ሁሉ አንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል፡፡ 


በመድረኩ የቀለአ'ድ የማኅበረሰብ አቀፍ የዱር እንሰሳት ጥብቅ ስፍራ ከየት ጀምሮ የት እንደ ደረሰ የተሰራውን ስራ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ወንዲፍራው ደጀኔ አቅርበዋል።


በመቀጠልም የጥብቅ ስፍራው ለቱሪዝም ልማት ያለውን አቅም እና ዕድሎች በተመለከተ ቦታው ድረስ በመገኘት የዘጋቢ-ፊልም በማዘጋጀትና የቴለቭዢን ሽፋን እንዲያገኝ በማድረግ ሰፊ የማስተዋወቅ ስራ በሰራው ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም ፅሁፍ የቀረበ ሲሆን በኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን ቢሮ ባለሙያዎች በሆኑት አቶ ምትኩ ገ/ሚካዬልና አቶ ታምራት ጫንያለው የተዘጋጀውን ረቂቅ የህግ ማዕቀፍና ጥበቅ ሥፍራውን ለመከለል የሚያስችሉ ስራዎችንና ሂደት በተመለከተ ለተሳታፊዎች ገለጻ አድርገዋል።


በመጨረሻም በቀረቡት ዶክመንቶች ላይ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተወክለው የተገኙ ተሳታፊዎች የተለያዩ ሃሳቦችን አንስተው ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡ በመድረኩ ላይ የአስተዳደሩ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ የማኅበረሰቡ ተወካዮች፣ ቢሮ ኃላፊዎች እና የዩኒቨርሲቲው ምሁራን ተሳትፈዋል፡፡ 


ቀለአ'ድ የሚለውን ስያሜ በጥብቅ ስፍራው አጠገብ ከምትገኘው እና ከድሬዳዋ ከተማ በስተሰሜን ምስራቅ በ45 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ባረፈችው ጥንታዊ ከተማ ያገኘ ሲሆን ቀለአ'ድ ለዘይላ ወደብ ቅርበት የነበራትና የድሬደዋ ከተማ ከመመስረቷ በፊት በ1870-1880ዎቹ በከተማዋ የመንግስት ቀረጥ የሚሰበሰብበት የጉሙሩክ መስሪያ ቤት የነበረ መካነ ቅርስ ነው። በዚህ ታሪካዊ ስያሜ የሚጠራው የቀለአ'ድ የማኅበረሰብ አቀፍ የዱር እንስሳት ጥብቅ ስፍራ ከ537 ስኩዬር ኪሎ ሜትር በላይ በሆነ ስፍራ ያረፈ በውስጡም ከ30 በላይ አጥቢ ዱር እንስሳት፣ 71 ገደማ የሚደርሱ የአእዋፍ ዝርያዎችንና ከ50 የሚበልጥ የዕፅዋት ዝርያዎችን እንደሚገኙ በአካባቢው የተሰሩ ጥናቶች ያመለክታሉ።

Share This News

Comment