የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በመንገድ ደህንነት፣ የትራፊክ አደጋ ቅነሳ፣ የመሰረተ ልማት እና የከተማ ልማት ቅየሳ ስራዎችን ከተለያዩ ክልሎች እና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ጋር በትብብር ለመስራት ተስማማ፡፡
ዩኒቨርሲቲው ከኢትዮጲያ መንገድ ደህንነት እና ኢንሹራንስ ፈንድ አገልግሎት፣ ከፌደራል ፓሊስ ኮምሽን፣ ከድሬዳዋ ፓሊስ ኮምሽን እና ከድሬዳዋ ትራንስፓርት እና ሎጅስቲክ ባለስልጣን ጋር የትራፊክ አደጋ መከላከል ስራዎች ላይ በትብብር ለመስራት ተስማምተዋል፡፡
ስምምነቱ በመንገድ ደህንነት እና ትራፊክ አደጋ ዙሪያ የሚሰሩ ችግር ፈቺ ምርምሮችን በጋራ ለመስራት፣ የመንገድ ደህንነትን የተመለከቱ ተግባራትን በጋራ ለመከወን፣ የአቅም ማሻሻያ ስልጠናዎችን በጋራ ለመስጠት፣ የመረጃ፣ እውቀት እና የባለሙያ ልውውጥ ለማድረግ የሚስችል መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የመንገድ ደህንነት እና የትራፊክ አደጋን ከመቀነስ አንጻር አገልግሎት የሚሰጡ እና ዘመናዊ አሰራርን የሚያረጋገጡ ቴክኖሎጂዎችን በማበልፀግ ለተለያዩ ተቋማት እያበረከተ መሆኑ ተነግሯል፡፡
በስምምነት ፕሮገራሙ ላይ የተገኙት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ም/ፕሬዝዳንት እና የፕሬዝዳንት ተወካይ የሆኑት ዶ/ር መገርሳ ቃሲም እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው በ2018 በጀት ዓመት በህገ ወጥ የሰው ዝውውር እና የትራፊክ አደጋን የመከላከል ስራዎችን ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ የተናገሩ ሲሆን ከተለያዩ ባለድርሻ አካላትም ጋር በትብብር ለመስራት ዩኒቨርሲቲው በሩ ክፍት መሆኑንም አመላክተዋል፡
Share This News