Logo
News Photo

ሁለተኛው ዙር ሴሚናር በድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ተካሄደ፡፡

ሁለተኛው ዙር ሴሚናር በዮኒቨርሲቲው የምርምር ህትመት፣ ዶክመንቴሽንና ስርጭት ዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት በድሬዳዋ ዮኒቨርሲቲ  ተካሄደ 

የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር መገርሳ ቃሲም በዚሁ ሴሚናር ላይ በመገኘት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በንግግራቸውም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ መምህራን ቁልፍ ሚና አላቸው ያሉ ሲሆን ለዚህም እርስ በእርሳቸው በመማማርና  በውይይቶች አቅማቸውን ማሳደግ  ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ዶ/ር መገርሳ የዚህ አይነት ሴሚናሮች በቀጣይነት መካሄዳቸው በዩኒቨርሲቲው የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለውን ጥረት ስኬታማ ለማድረግ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ጠቁመው መምህራንም በተለይ የትምህርት ጥራት ላይ እክል የሚፈጥሩ ክፍተቶችን በመሙላት የበኩላቸውን ይወጡ ዘንድ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የምርምር ህትመት፣ ዶክመንቴሽንና ስርጭት ዳይሬክቶሬት ዳሬክተር ዶ/ር መሐመድ ቃሶ በበኩላቸው የዚህ አይነቱ ሴሚናር ከዚህ ቀደም  በተደጋጋሚ በኮሌጅ ደረጃ ይካሄድ የነበረ መሆኑን ጠቅሰው ይህ ሴሚናር በ2014 በጀት አመት በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ለሁለተኛ ጊዜ መደረጉንና ከተለያዩ  የትምህርት ክፍል የተውጣጡ መምህራን በሴሚናሩ ላይ ጥናታዊ ጽሁፋቸውን እንዳቀረቡ ተናግረዋል፡፡

በዚህ ግማሽ ቀን በቆየው ሴሚናር ላይ አራት ጥናታዊ ጽሁፎች በዩኒቨርሲቲው መምህራን ቀርበው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን በሴሚናሩ ላይ ቁጥራቸው ከ80 በላይ የሚሆን መምህራን ተሳትፈውበታል።

Share This News

Comment