Logo
News Photo

ውሎና አዳራቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ ህፃናትን ችግርን በዘላቂነት መቅረፍ ላይ ትኩረቱን ያደረገ የፓናል ውይይት ተካሄደ፡፡

የፓናል ውይይቱን ኤስ.ኦ.ኤስ የህፃናት መንደር ከድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ሲሆን በፓናል ውይይቱ ላይ በመገኘት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት  በድሬዳዋ አስተዳደር ሴቶችና ህፃናት ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የማኅበራዊ ጉዳዮች ዘርፍ ኃላፊ  አቶ አብዱረህማን ሙሳ ሲሆኑ በንግግራቸውም  እንደ ሀገር ውሎና አዳራቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ ህጻናት ቁጥር አሁን ላይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ጠቁመው በተለይ ድሬዳዋ ለጅቡቲ ወደብ ቅርብ መሆኗ በፍልሰት ወደ ከተማዋ በመግባት ውሎና አደራቸውን በጎዳና ላይ የሚያደርጉ ህፃናት ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንደመጣና ህጻናቱ የሚገጥማቸው ችግርም ውስብስብ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ይሄንን ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ወሳኝ ነው ያሉት አቶ አብዱረህማን በተለይ ምሁራን በችግሩ ዙሪያ የተለያዩ ጥናትና ምርምሮችን በማድረግ የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በኤስ.ኦ.ኤስ የህፃናት መንደር የሐረር የህፃናት መንድር ፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ አንዱአለም ጌታቸው ኤስ.ኦ.ኤስ  ከተመሠረተ  የ75 ዓመት ዕድሜን  ያስቆጠረ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት እንደሆነና በሀገራችን ኢትዮጵያም ድርጅቱ 50ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በቅርቡ ማክበሩን አስታውሰው ድርጅቱ ለአምስት አስርት ዓመታት በዘለቀው አገልግሎቱ በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረጉ ውጤታማ ተግባራትን ማከናወኑን ገልጸዋል።

እንደ አቶ አንዱአለም ገለጻ በአሁኑ ጊዜ ኤስ ኦ ኤስ የህጻናት መንደር ሀረር ፕሮግራም በምስራቁ የሀገራችን ክፍል በሐረር ፣ በድሬዳዋ፣ በምስራቅና በምዕራብ ኦሮሚያ እንዲሁም በከፊል የሶማሌ ክልል ቁጥራቸው ከ57 ሺህ የሚበልጡ  የማኅበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ የቻሉ ፕሮጀክቶች ቀርጾ ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝና ድርጅቱ  ካለፈው 2 ዓመት ወዲህ ከፎረም ኦን ሰስቴነብል ችልድረን ኢንፓወርመንት ከተባለ ሀገር በቀል ግብረሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር በድሬዳዋ ውሏቸውንና አዳራቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ ህፃናትን ህይወት የሚቀይሩ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ እየሰራ እንደሚገኝና በዚህም አጠቃላይ ቁጥራቸው ከ2700 በላይ የሚሆኑ ህፃናትን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት እየተገበረ መሆኑን ገልፃዋል።

በፓናል ውይይቱ ላይ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የህግ ኮሌጅ መምህርና ተመራማሪ የሆኑት መምህር አለምስገድ ደጀኔ 'የህጻናት መብቶች ተጋላጭነትታቸው የመፍትሄ አቅጣጫዎች' በሚል ርዕስ እንዲሁም በኤስ.ኦ.ኤስ የህፃናት መንደር የድሬደዋ የፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ሚካኤል ስንታየሁ 'ውሎና አዳራቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ ህፃናት ተጋላጭነት ያለበት ደረጃ ፣ የተጋላጭነት ዋነኛ ምክንያት እና ተጋላጭነታቸውን ለመቀነስ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች' በሚል ርዕስ ጽሁፎችን አቅርበው  ከተሳታፊዎች የተለያዩ ሃሳቦችና አስተያየች ተሰጥቶባቸዋል።

በመጨረሻም የዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ ተሳትፎ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ወንዲፍራው ደጀኔ የመዝጊያ ንግግር ያደረጉ ሲሆን ተቋሙ እየሰራ ላለው ስራ አመስግነው ችግሩ ሥር የሰደደና በየግዜው ተለዋዋጭ በመሆኑ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ትብብር ቅንጅትና ቁርጠኝነት የሚፈልግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲም እንደ ባለድርሻ አካል ሃላፊነቱን እንደሚወጣና አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል ገብተው  የፓናል ውይይቱ ተጠናቋል፡፡


Share This News

Comment