የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በዶሮ እርባታ ሥራ ተደራጅተው ለሚሰሩ ወጣቶች የጫጩትና የመኖ ድጋፍ አደረገ።
ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በቀበሌ 02 በተለምዶ መርመርሳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በማኅበር ተደራጅተው በዶሮ እርባታ ሥራ ለተሠማሩ ወጣቶች ድጋፍ ያደረገ ሲሆን በድጋፍ ርክክብ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ተወካይና የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶ/ር መገርሳ ቃሲም ከዚህ ቀደም ዩኒቨርሲቲው በማኅበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ በርካቶችን ተጠቃሚ ያደረጉ ተግባራት ማከናወኑን አስታውሰው ይህ ዛሬ የተደረገው ድጋፍም በዋነኝነት ሥራ እጥ ወጣቶችን ትኩረት ያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝደንት ዶ/ር ተማም አወል በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰቡን ችግሮች ለመቅረፍ ከምንግዜውም በላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረው ዛሬ የተደረገው ድጋፍም ወጣቶቹ ያላቸውን ጥሪት በማሰባሰብ ዩኒቨርሲቲው ተጨማሪ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው በጠየቁት መሰረት የተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ዶ/ር ተማም አያይዘውም ዩኒቨርሲቲው በቀጣይ ወጣቶቹ ውጤታማ እንዲሆኑና ለሌሎች ሥራ እጥ ወጣቶች የስራ ዕድል እንዲፈጥሩ ሙያዊ ድጋፍና ክትትል ማድረጉን ይቀጥላል ብለዋል፡፡
የተደረገውን የድጋፍ አይነት በተመለከተ የዪነቨርሲቲው ማኅበረሰብ ተሳትፎ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ወንዲፍራው ደጀኔ ሲያብራሩ ለአካባቢው ወጣቶች የተደረገው ድጋፍ በአይነት 335 (ሶስት መቶ ሰላሳ አምስት) የ40 ቀን ጫጩቶች እና የ4 ወር መኖ መሆኑን ጠቅሰው ይህም በብር ሲተመን ከ210 ሺህ (ሁለት መቶ አሥር ሺህ ) ብር በላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ድጋፍ የተደረገላቸው ወጣቶች የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ላደረገላቸው ድጋፍ አመስግነው ይህ የተደረገላቸው ድጋፍ የተሻለ ሥራና ስኬት እንዲጎናጸፉ ከማስቻል ባሻገር ወጣቶቹ ከራሳቸው አልፈው ለሌሎችም የስራ ዕድል መፍጠር እንዲችሉ መንገድ የሚከፍትላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
Share This News