ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በየካቲት ወር 2016 ዓ.ም ለተሰጠው ሃገር አቀፍ የመውጫ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ኮሌጆች እና ለቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት እውቅና ሰጠ፡፡
በፕሮግራሙ ላይ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር መገርሳ ቃሲም የመክፈቻ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በንግግራቸውም ይህ ውጤት የተመዘገበው የዩኒቨርሲቲው ከፈተኛ አመራሮች፤ ኮሌጆች፤ትምህርት ክፍሎች እና መምህራን በሃግር አቀፍ ደረጃ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት በጋራ ተባብረው እና ተናበው በመስራታቸው መሆኑን አመልክተዋል፡፡ በመቀጠልም ዶ/ር መገርሳ ቃሲም በዚህ አመት ለተመዘገበው ከፍተኛ ውጤት ምስጋና በማቅረብ ወደፊት ለሚሰጠው የመውጫ ፈተና ከዚህ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ሁሉም አካላት ጠንክረው እንዲሰሩ መልዕክት በማስትላልፍ ዩኒቨርሲቲው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ በማድረግ ከጎናቸው እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡
በመቀጠልም የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ሁሴን መሀመድ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በንግግራቸውም ለተመዘገበው ከፍተኛ ውጤት መሳካት ምክያቱ ኮሌጁ የሰጠውን 100% የማሳለፍ እቅድ ሁሉም ትምህርት ክፍሎች እቅድ አውጥተው ፈተና ካስፈተኑ 5 ት/ክፍሎች መካካል 4 ት/ክፍሎች 100% ያሳለፉ ሲሆን አጠቃላይ ፈተና ከወሰዱ 152 ተማሪዎች ውስጥ 150 (98.7%) ማለፋቸውን ገልጸው ይህ ውጤት እንዲመጣ ከፈተኛ አስተዋፅዖ ላደረጉ የትምህርት ክፍል ሃላፊዎች እና መምህራን ከፍተኛ ምስጋና በማቅረብ በሚቀጥለው ለሚሰጠው የመውጫ ፈተናም ሁሉም ት/ክፍሎች 100% ለማሳለፍ ጠንክረው እንዲሰሩ እና ኮሌጁም ከፍተኛ ድጋፍ እና ክትትል እንደሚያደርገላቸው አመልክተዋል፡፡
በመቀጠልም የማህበረሰብ እና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ማዕዛሽወርቅ እርገጥ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በንግግራቸውም በዚህ አመት የተመዘገበው ከፍተኛ ውጤት በኮሌጁ እና ትምህርት ክፍሎች በተደረገ ከፍተኛ ጥረት መሆኑን ገልጸው ወደፊትም በሰኔ ወር ለሚሰጠው የመውጫ ፈተና ከዚህ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገበ ኮሌጁ ጠንክሮ እየሰራ መሆኑን ገለጸዋል፡፡
በፕሮግራሙ የተመረቁ ተማሪዎች እና በሚቀጥለው ዙር የመውጫ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎች የተገኙ ሲሆን ተመራቂ ተማሪዎች የኮሌጆችን ጥረት በማድነቅ ልምዳቸውን ፈተና ለሚወስዱ ተማሪዎች አካፍለዋል፡፡ በፕሮግራሙ ላይ የተገኙ በሚቀጥለው የመውጫ ፈተና የሚውስዱ ተማሪዎች ደግሞ ይህ ፕሮግራም ከፍተኛ መነሳሳት እንደፈጠረላቸው በመግለጽ እነሱም የተሻለ ውጤት እንደሚያስመዘግቡ ቃል ገብተዋል፡፡
Share This News