ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ እና ገበያ ቴክኖሎጂ የተባሉ ተቋማት በዩኒቨርሲቲው ለሚገኙ ተማሪዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጡ።
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ቴክኖሎጂ ኢንኩቤሽን ማዕከል ባዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ላይ ከሳፋሪኮም ኢትዮጵያ እና ገበያ ቴክኖሎጂ ከተባሉ ተቋማት የመጡ ባለሙያዎች በዩኒቨርሲቲው ለሚገኙ ተማሪዎች በስራ እድል ፈጠራ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጡ።
በመድረኩ ላይ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ እና ገበያ ቴክኖሎጂ የተባሉት ድርጅቶች ስለሚሰጧቸው አገልግሎቶች አጠቃላይ ገለጻ የተደረገ ሲሆን ድርጅቶቹ ከዚህ ቀደም በአንደኛው ዙር በሀገር አቀፍ ደረጃ ቁጥራቸው 50 ለሚሆኑ ሰልጣኞች 'Software Development Training' በሚል ፕሮግራም የሶፍትዌር ልማት ስልጠና በመስጠት 26 ሰልጣኞችን በሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ድርጅት ውስጥ እንዲሰሩ እንዲሁም የቀሩት ደግሞ የራሳቸውን ስራ ፈጥረው እንዲሰሩ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
በዚህ በሁለተኛው ዙር የስልጠና ፕሮግራም ድርጅቶቹ 'Safaricom Talent Cloud' በሚል ርዕስ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ለሚገኙ ተማሪዎች ስልጠና ያዘጋጁ ሲሆን በመጀመሪያው አመት ቁጥራቸው 10 ሺህ ለሚደርሱ ተማሪዎች በCyber security, AI & Data science, Software Development, Project Management, Digital Marketing, Business Analyst እና በተለያዩ የስልጠና ርዕሶች ላይ ስልጠና ለመስጠት ያቀዱ ሲሆን ተማሪዎችም በ http://safaricom.gebeya.com በሚለው ማስፈንጠሪያ በመግባት እንዲመዘገቡና አስፈላጊውን መስፈርት በማሟላት ስልጠናውን እንዲወስዱ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
ይህ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሀ-ግብር ከዚህ ቀደም በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ስራ መፍጠር የሚያስችል ሃገራዊ የክህሎት ስልጠና የማስጀመሪያ መርሀ-ግብር ላይ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ከሳፋሪኮም ኢትዮጵያ እና ገበያ ቴክኖሎጂ ከተባሉ ሁለት ተቋማት ጋር በጋራ ለመስራት የተፈራረመው የስምምነት ሰነድ አካል እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል።
Share This News