Logo
News Photo

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በዋናው የመግቢያ በር በኩል በ9.1 ሚሊየን ብር የታክሲ ተርሚናል ለመገንባት ሸሁት ከተባለ የግል የህንፃ ተቋራጭ ጋር የውል ስምምንት ተፈራረመ፡፡

በዩኒቨርሲቲው ዋናው የመግቢያ በር በኩል የሚገነባው የታክሲ ተርሚናል በ885 ካሬ መሬት ላይ የሚያርፍ ነው፡፤

የታክሲ ተርሚናሉ ሸሁት የተባለ አጠቃላይ የህንፃ ተቋራጭ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በገባው ውል መሠረት በ9 ሚሊየን 181 ሺህ ብር የሚገነባ ሲሆን በውስጡም የታክሲ ፌርማታ ፣ የካፍቴሪያ ፣ የመኪና እጥብት ፣ የሸቀጣሸቀጥ መሸጫ ሱቆች ፣ የህዝብ መፀዳጃ ቤት እና የተለያዩ የመዝናኛ መዕከላት የያዘ መሆኑን በውል ስምምነቱ ላይ ተገልጿል፡፡

በዚሁ ፕሮግራም ላይ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም የታክሲ ፌርማታው ግንባታ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያለው መሆኑን ጦቁመው ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ባሻገር ማህበረሰብ ተኮር ስራዎችን በመስራት አካባቢውን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ጦቁመዋል፡፡

የተርሚናሉ ግንባታ የአካባቢውን ገፅታ ውበት ከማላበስ ባለፈ ለበርካታ የአካባቢው ወጣቶች እና ሴቶች የሥራ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል፡፡

የአካባቢ ልማት እና ህብረተሰብ ተሳትፎ ኤጀንሲ ሀላፊ ወ/ሮ ረሂማ አወል ይህ የታክሲ ተርሚናል ፕሮጀክት አስተዳደሩ ከተማዋን ፅዱ፣ ውብ እና ምቹ አካባቢን ለመፍጠር እያደረገ ላለው እንቅስቃሴ ማሳያ ነው ብለዋል።

ወ/ሮ ረሂማ አክለውም ይህ ፕሮጀክት ከጅማሬው እስከ ማጠናቀቂያው ድረስ የአካባቢው ማህበረሰብ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አማካሪ እና የማህበረሰብ ዘርፍ ሀላፊ አቶ ዑመር አህመድ ዩኒቨርስቲው እያደረገ ላለው የማህመረሰብ ተኮር ስራዎች አመስግነው ፕሮጀክቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እና ክትትል እንደሚያደርግ ገልፀዋል።

የሸሁት የግል የህንፃ ተቋራጭ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮሐንስ አባቱ በበኩላቸው የተርሚላኑን ግንባታ በውላቸው መሠረት በተቀመጠው የ6 ወር ጊዜ አጠናቀው ለዩኒቨርሲቲው የሚያስረክቡ መሆኑን በዚሁ ወቅት ተናግረዋል፡፡

Share This News

Comment