አመታዊው የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ሰራተኞች የእግርኳስ ውድድር በቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ቢ ቡድን አሸናፊነት ተጠናቀቀ፡፡
በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት ከግንቦት 13 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ለአንድ ወር ያህል ሲያካሄድ የነበረው ዓመታዊው የዩኒቨርሲቲያችን ሰራተኞች የተሳተፉበት የእግር ኳስ ውድድር የእለቱ የክብር እንግዶች ዶ/ር ተማም አወል የም/ቴ/ሽ ም/ፕሬዝዳንት፣ ዶ/ር ሰለሞን ዘሪሁን የአስ/ል/ም/ፕሬዝዳንት እንዲሁም ዶ/ር መገርሳ ቃሲም የአካ/ጉ/ም/ፕሬዝዳንት በተገኙበት በዛሬው እለት ፍጻሜውን አግኝቷል፡፡
በፍጻሜ ውድድሩ ላይ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ቢ ቡድን ከቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ኤ ቡድን ጋር የተገናኙ ሲሆን ቡድኖቹ በመደበኛ ክፍለ ጊዜ ጨዋታውን 2-2 በማጠናቀቃቸው ወደመለያ ምት (Penality) ያመሩ ሲሆን የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ቢ ቡድን በመለያ ምት ተጋጣሚውን በማሸነፍ የዋንጫ ባለቤትና የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ መሆን ችሏል፡፡
ውድድሩን በሁለተኝነት ያጠናቀቀው የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ኤ ቡድን የብር ሜዳሊያ እንዲሁም በሶስተኝነት ያጠናቀቀው የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ቡድን ደግሞ የነሃስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆነዋል። ሌላኛው በውድድሩ የተካፈለው የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቡድን የፀባይ ዋንጫ ተሸላሚ የሆነ ሲሆን አብርሀሌ ፍሰሀ ከቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ኤ ቡድን ኮከብ ተጫዋች፣ አላዛር አብርሀም ከቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ኤ ቡድን ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ፣ ምስጋና ሙጬ ከቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ቢ ቡድን የውድድሩ ምርጥ በረኛ እንዲሁም አቶ ተመስገን አለማየሁ ከቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ኤ ቡድን ምርጥ አሰልጣኝ በመሆን የተመረጡ ሲሆን ሽልማታቸውንም ከእለቱ የክብር እንግዶች እጅ ተቀብለዋል።
Share This News