የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ለእንድ ወር ሲያሰለጥናቸው የነበሩ የግቢ የፀጥታና ደህንንት አባላትን አስመረቀ፡፡
በምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ የተገኙት የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ የተከበሩ ክቡር አቶ ከድር ጁሃር እንደገለጹት ድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ብቁና የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት የተሰጠውን ሃገራዊ ተልዕኮ ማሳካት እንዲችል የግቢውን ፀጥታና ደህንነት እንዲጠበቅ የሚያደርገውን ጥረት አስተዳደሩ በሚፈለገው ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸው በተለይም የዩኒቨርሲቲውን የፀጥታ ሁኔታ ዘመኑ ባፈራቸው ቴክኖሎጂዎች ታግዞ አስተማማኝ ማድረግ እንዲችል ጥረት እንደሚደረግም ተናግረዋል፡፡
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም በበኩላቸው እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው በሃገሪቱ የተከሰተውን የመንግስት ለውጥ ተከትሎ የመማር ማስተማሩ ሂደት ከመስተጓጎል አልፎ ሙሉ ለሙሉ አስከመቋረጥ ደርሶ እንደነበር አስታውሰው ከባለፉት ዓመታት ወዲህ ግን በተሰራ በርካታ ተግባራት የግቢውን የፀጥታ ሁኔታ በእጅጉ መሻሻል ከማስቻሉም ባለፈ የመማር ማስተማር ሂደት ሰላማዊ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡ ይህንንም ሰላማዊ የሆነ የግቢ የፀጥታ ሁኔታ በዘላቂነት ለማረጋገጥ ዩኒቨርሲቲው ከህብረተሰቡ እና ከአጋር አካላት ጋር የጀመረውን አበረታች ተግባር አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
በዝግጅቱ ላይ የተገኙት የድሬደዋ ፖሊስ ኮምሽን ኮምሽነር አለሙ መግራ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው የግቢውን ሰላምና ጸጥታ በዘላቂነት አስተማማኝ የማድረግ እንቅስቃሴ ኮምሽኑ እያደረገ ያለውን ድጋፍና ተቀራርቦ የመስራት ተግባር አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ የግቢ ፀጥታና ደህንንት አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት ሻምበል ተመስገን ደሳለኝ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ስልጠናው የማኅበራዊ ሳይንስ፣ የፀጥታ ጥበቃ ሳይንስ እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆኑን ጠቁመው በዩኒቨርሲቲው ለመጀመሪያ ዙር ስልጠና ወስደው የተመረቁት የግቢ ፖሊስ አባላትም በቀጣይ የግቢውን የፀጥታ ሁኔታ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ ለማስጠበቅ የሚደረገውን ጥረት እንዲሳካ አቅም የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡
በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ በስልጠናቸው ወቅት የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ ሰልጣኞች እና ስለጠናውን ሲሰጡ ለነበሩ አካላትና ግለሰቦች የእወቅና የማበረታቻ ሽልማት ከእለቱ የክብር እንግዶች ተበርክቶላቸዋል፡፡
Share This News