Logo
News Photo

በምርምር መረጃ አያያዝ፣ አስተዳደርና አጠቃቀምን በተመለከተ ለድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ስልጠና ተሰጠ፡፡

በዩኒቨርሲቲው የምርምር ህትመት፣ ዶክመንቴሽንና ስርጭት ዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት በምርምር መረጃ አያያዝ፣ አስተዳደርና አጠቃቀም (Research Data Management and Utilization) ዙርያ ለሁለት ቀናት የቆየ ስልጠና ለዩኒቨርሲቲው መምህራን ተሰጠ። 

ስልጠናው ለተመራማሪዎች እና ለዩኒቨርሲቲው የሚኖረውን ፋይዳ በተመለከተ የዩኒቨርሲቲው የምርምር ህትመት፣ ዶክመንቴሽንና ስርጭት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ሙሐመድ ቃሶ ገለፃ ያደረጉ ሲሆን ስልጠናውን በንግግር የከፈቱት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሰለሞን ዘሪሁን ናቸው። 

ዶ/ር ሰለሞን በንግግራቸው ላይ ይህ ስልጠና ጽንሰ ሃሳብንና ተግባርን አጣምሮ የያዘ ስለሆነ ተመራማሪዎች በቀጣይ ለሚሰሯቸው የጥናትና ምርምር ስራዎች በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ገልፀው ሰልጣኝ መምህራን ከስልጠናው የሚያገኙትን እውቀት ተጠቅመው  የተለያዩ ጥናትና ምርምሮችን በማድረግ ከአካባቢያቸው አልፈው ሃገርን ሊጠቅም የሚችል ስራ መስራት እንዲችሉ ታሳቢ ተደርጎ የተዘጋጀ ስልጠና ስለሆነ መምህራን ስልጠናውን በትኩረት እንዲከታተሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ 

በዚህ ለሁለት ቀናት በቆየው ስልጠና  ላይ መረጃን እንዴት በአግባቡ ማስተዳደርና መጠቀም እንደሚቻል፣ የምርምር ስራን ታዋቂ በሆኑ ጆርናሎች  ላይ በክፍያም ሆነ ያለክፍያ እንዴት ማሳተም እንደሚቻል፣ የተለያዩ ዓይነት ጆርናሎችን መለየት የሚቻልባቸው መንገዶች፣ ክፍት የሆኑ መረጃዎችና ምሁራዊ የመገናኛ መሳሪያዎች አጠቃቀም እና በሌሎች ተያያዥነት ባላቸው ርዕሰ-ጉዳዩች ላይ ለመምህራን ስልጠና ተሰጥቷል፡፡ 

ስልጠናው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመጡት ዶ/ር መልካሙ በየነ የተሰጠ ሲሆን በስልጠናው ላይ ከተለያዩ ትምህርት ክፍሎች የተውጣጡ ቁጥራቸው ከ90  በላይ የሆኑ መምህራን ተካፋይ እንደሆኑበት ለማወቅ ተችሏል።

Share This News

Comment