የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ከኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት ኢትዮጽያ ጋር በመተባበር “Executive Masterclass on Public Entrepreneurial Innovation and Ecosystem Building” ላይ ከፍተኛ አመራርን ጨምሮ በየደረጃው ለሚገኙ አመራሮች ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ተጠናቀቀ፡፡
በስልጠናው መክፈቻ ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም የዩኒቨርሲቲያችን ርዕይ እውን ለማድረግ በየደረጃው ያለው አመራር ዘመኑ የሚጠይቀውን ዕውቀትና ክህሎት ተጠቅሞ ችግሮችን ወደ መልካም አጋጣሚ የመቀየር ሚናውን ማሳደግ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ይሄንኑ መሠረት በማድረግና ዩኒቨርሲቲው ወደ አፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲነት የሚያድርገውን ሽግግር ሙሉ ለሙሉ እንዲሳካ በማድረግ ተወዳዳሪነቱንና ተመራጭንቱን ለማጉላት በተለይ በየደረጃው ያሉ አመራሮች ውሳኔ ሰጪነትን ለማጎልበት ያስችል ዘንድ ስልጠናው መዘጋጀቱን ገልጸው በየደረጃው ሁሉም ሰልጣኝ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ አስገንዝበዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ተቋሟዊ ለውጥና መልካም አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና የስልጠናው አስተባባሪ የሆኑት ዶ/ር መላኩ ማስረሻ በበኩላቸው በሁለት ዙር ተከፍሎ ሲሰጥ የነበረው ስልጠና Entrepreneurship Development Institute (EDI) - Ethiopia ጋር በመተባበር የተዘጋጀ መሆኑን ጠቅሰው ስልጠናው በተለይም በዩኒቨርሲቲው በቅርቡ የተሠራውን የሰራተኛ የስራ ድልደላ መዋቅርን ተከትሎ ወደ አመራርንት የመጡ ሠራተኞችን የአመራርንት ክህሎት ለማሳደግ የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ዶ/ር መላኩ አክለውም ስልጠናው በተለይም የዩኒቨርሲቲውን ርዕይና ተልዕኮ ተረድቶ በቀጣይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ዕውቀትና ክህሎትን ተጠቅሞ በመፍታት ወደ ሚፈለገው ግብ ላይ ለመድረስ በቂ የሆነ አቅም ለአመራሩ ለመፍጠር ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑንም ጨምረው ገልፀዋል፡፡
በመጨረሻም ስልጠናው በሁለት ዙር ተከፍሎ የተዘጋጀና በመጀመሪያ ዙር ስልጠና በቁጥር ሐምሳ ስምንት (58) ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች ስልጠናውን የወሰዱ ሲሆን በሁለተኛው ዙር ደግሞ በቁጥር አንድ መቶ ሁለት (102) የቡድን መሪዎች፣ የትምህርት ክፍል ኃላፊዎች እና የአካዳሚክ አስተባባሪዎች የተዘጋጀውን ስልጠና መውሰዳቸው ታውቋል፡፡
Share This News