የመጀመሪያው ዓመታዊ የካይዘን ፎረም
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ጋር በመተባበር አምራች ኢንዱስተትሪዎችና ተቋማት በካይዘን የአመራር ፍልስፍና በመታገዝ የተቀናጀ አሰራርን በመከተል የምርትና የአገልግሎትን ጥራትን በማስጠበቅ በሚሰጠው አገልግሎት ተጠቃሚውን ማርካትና ተወዳዳሪ መሆን እንዲችሉ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የሚያስችል ዓመታዊ የካይዘን የምክክር መድረክ አምራች ኢንዱስትሪዎች፣ የከተማ አስተዳደሩ ተጠሪ ተቋማት እና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ "ካይዘን ለዘላቂ ለውጥ" በሚል መሪ ቃል ተካሂዷል፡፡
በመድረኩ ላይ በመገኘት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ገደፋየ፤ ካይዘን ብዙ ሃገራት ተጠቅመውበት ለውጣቸውን እውን አድርገውበት ያየነውና በትንሽ ጥረትና በብዙ ተሳትፎ ብዙ ድምር ለውጦችን ማስመዝገብ የሚያስችል የለውጥ መሳሪያ በመሆኑ አምራች ኢንዱስትሪዎች የምርት ጥራትንና ምርታማነትን በመጨመር ተወዳዳሪና ተኪ ምርቶችን ለማምረት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሁሉ ቁልፍ ሚና እንዳለው በመገንዘብ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከዩኒቨርሲቲያችን ጋር በጋራ እየሰሩ እንደሚገኙ በመግለፅ ይህን ጅምር በዘላቂነት በማስቀጠል በአስተዳደሩ ሞዴል ኢንዱስትሪዎችን ለማፍራት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትብብር መስራት እንዳለባቸው ገልፀዋል፡፡
በመቀጠልም የአስተዳደሩ የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊና የአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪ ኢንዱስትሪ ልማት ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ አብዲ ሙክታር ሙሜ፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ የማምረት አቅምን ለማሳደግ በተደረገው ጥረት ከ38 ወደ 59% ማደጉን፣ በአስተዳደሩ ከምርት ብክነት ጋር በተያያዘ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ በተደረገው ጥረት 53% መድረሱን የገለፁ ሲሆን የውጭ ገቢ ምርቶችን በመቀነስ ተኪ ምርቶች ላይ ትኩረት በማድረግ የምርት ጥራት ማሻሻያ ላይ በትኩረት መስራት አስፈላጊ መሆኑን በመጥቀስ ዘርፉን ለመደገፍና ብቁ የሰው ኃይልን ለማፍራት ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመቀናጀት በርካታ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኝ በመግለፅ የውይይት መድረኩን አስጀምረዋል፡፡
በመጨረሻም ለውይይት መነሻ የሚሆኑ አራት ተሞክሮን የሚያሳዩ ፅሁፎች ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ፣ ከድሬዳዋ አስተዳደር የካይዘን ኢንስቲትዩትና ከኢትዩጵያ የካይዘን የልህቀት ማዕከል በመጡ ባለሙያዎች ከቀረቡ በኋላ ሰፊ ውይይት በማካሄድና በካይዘን ዙሪያ በካይዘን ኢንስቲትዩት እና በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የተሰሩ ስራዎችም በተዘጋጀው የፎቶ ኢግዚቢሽን በተሳታፊዎች እንዲጎበኙ በማድረግ ፕሮግራሙ ተጠናቋል።
Share This News