Logo
News Photo

ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የአንድ ሳምንት የትምህርት መርሃግብር ለኢንደስትሪ ባለሙያ ”one week class for industry experts” የሚል መረሃግብር በመቅረፅ የኢንደስትሪ ባለሙያዎች በመማር ማስተማሩ ተግባር ላይ እንዲሳተፉ የማድረግ ስራ አሰጀመረ፡፡

ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ አፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርስቲ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የሚጠበቅበትን ተግባር ተኮር ትምህርት ከማሳካት አንጻር የመማር ማስተማር ስራው ላይ የኢንደስትሪ ባለሙያዎችን በተለየ ፕሮግራም ማሳተፍ መጀመሩን በዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ልዩ ረዳት የሆኑት ዶ/ር ግርማ ቤካ ተናግረዋል። 

የአካዳሚክ ም/ፕሬዝዳንት ጽ/ቤቱ ከኢንደስትሪ ትስስር ቢሮ ጋር በመተባበር "የአንድ ሳምንት ክላስ ለኢንደስትሪ ባለሙያ" በሚል መሪ ቃል ከተለያዩ አምራችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የተጋበዙ ብቁ ባለሙያዎች ለአንድ ሳምንት በተመረጡ ኮርሶችና ርእሶች ላይ ከታህሳስ 14 - 18/2017 ዓ.ም ድረስ ተማሪዎችን ተግባር መር ትምህርት እንዲያስተምሩ የሚያደርግ ፕሮግራም መሆኑን ተገልጿል።  ይህ ፕሮግራም ዩኒቨርስቲው በቀጠናው ካሉ አምራችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር ጠንካራ ቤተሰባዊ ግንኙነት ለመመስረት የበኩሉን አስተዋጽኦ ከማድረጉ ባሻገር ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን ብቁ የሰው ሃይል ከማፍራት አንጻር የኢንደስትሪው ድርሻ ከፍተኛ በመሆኑ ተቋማት የወደፊት ሰራተኛቸውን ስራው በሚፈልገው ደረጃ የሚቀርጹበት ጥሩ አጋጣሚ ስለሆነ አምራችና አግልግሎት ሰጪ ተቋማት በዚህ ፕሮግራም በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ ቀርቧል።

በዚህ የአንድ ሳምንት የኢንደስትሪ ባለሙያ የመማር ማስተማር ተሳትፎ የዩኒቨርስቲውን ጥሪ ተቀብለው ተማሪዎችን በተግባር ለማስተማር ባለሙያ ለላኩ አምራችና አግልግሎት ሰጪ ተቋማት ዩኒቨርስቲው ያለውን አድናቆት የገለጹት የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝዳንት ተወካይ የሆነት ዶ/ር ጂብሪል አብዱልቃድር ይህ ፕሮግራም እንደ አፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ በመሆኑ ዩኒቨርስቲው የምሩቃንን የተግባር ክፍተት በመሙላትና የስራ ብቃት በማሳደግ ለኢንዱስትሪው የሚመጥን ግብአት ለማፍራት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይበት ነው ብለዋል። 

በመጨረሻም በዚህ ፕሮግራም የዩኒቨርስቲውን ግብዣ ተቀብለው አብረው ለመስራት ባለሙያዎችን የመደቡ ተቋማትን በማመስገን ባለሙያዎቹ ከተማሪዎቻችን ጋር መልካም ቆይታ እንዲኖራቸው የተመደበው አስተባባሪ ቡድን አስፈላጊውን የድጋፍ እንቅስቃሴ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።


Share This News

Comment