የድሬደዋ ዩንቨርሲቲ አቅዶ ከሚሰራቸው ቁልፍ ጉዳዮች መሃል አንዱ የማህበረሰቡን ባህል እና ቅርስ ተጠብቀው እንዲቆዩ እንዲሁም ለሚቀጥለው ትውልድ በተገቢው መንገድ እንዲተላለፉ ማድረግ ሲሆን ይህንኑ ስራ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለድሻ አካላት ጋር በትብብር ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ዛሬ በድሬደዋ ዩንቨርሲቲ ተከናውኗል።
ስምምነቱ የተደረገው በድሬደዋ ዩንቨርሲቲ፣ የድሬደዋ ከተማ ባህል እና ቱሪዝም ጽ/ቤት፣ በኦሮሚያ ጥናት ኢንስቲትዩት እና በፌደራል ቅርስ ባለስልጣን መካከል እንደሆነ ተነግሯል። በፊርማ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የዩንቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም የድሬደዋ ዩንቨርሲቲ የማህበረሰቡ ባህል፣ ታሪክ እና ቅርስ ተጠብቆ እንዲቆይ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና እንዲያገኙ አበክሮ ይሰራል ያሉ ሲሆን ዛሬ የተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ ዩንቨርሲቲው ለጀመረው የቅርስ ጥናት፣ ጥበቃ እና ማስተዋወቅ ስራ ትልቅ ግብዓት እንደሚሆን ተናግረዋል።
በ ቅርሶች ዙሪያ ለሚሰሩ የምርምር እና ጥበቃ ስራ ድርሻ ወስደው ከዩንቨርሲቲው ጋር በትብብር ለመስራት የተስማሙት የኦሮሚያ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ድሪባ ተረፋ በበኩላቸው ‘ ተቋማቸው ዩንቨርሲቲው የጀመረውን ትልቅ አላማ ያነገበ ስራ በፋናንስ እና በቁሳቁስ ለመደገፍ ፍላጎት እንዳለው በመግለጽ ቅርሶች የሀገር ሃብት እንዲሆኑ ከሃገርም አልፈው በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ኖሯቸው ተጨባጭ ፋይዳዎችን እንዲያስገኙ መሰራት እንደሚገባው ጠቁመዋል። በተለይ የሸጎዬ ባህላዊ ጭፈራ ትልቅ ማህበራዎ ፋይዳ ያለው እና እስከ አሁንም ድረስ በሀረርጌ ማህበረሰብ ዘንድ እሴት ሆኖ መቆየት የቻለ ባህላዊ ቅርስ እንደመሆኑ በቂ ጥናት እና ምርምር በዚሁ ባህል ዙሪያ ሊሰራ እንደሚገባ አስረድተዋል።
በዚሁ የፊርማ ስነ ስርዓት ላይ የኦሮሚያ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ድሪባ ተረፋ ተቋማቸው ከዚህ በፊት አንድ ሺህ (1000) የሚጠጉ መጽሃፍትን ለድሬደዋ ዩንቨርሲቲ ማበርከቱን አውስተው በቀጣይም ለመማር ማስተማር አገልግሎት የሚውሉ እስከ አምስት ሺህ (5000) የማስተማሪያ መጽሃፍትን እንደሚለግሱ ቃል ገብተዋል።
የመግባቢያ ስምምነት ሰነዱን የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ባህል እና ቱሪዝም ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ሚካኤል እንዳለ የፈረሙ ሲሆን የእርሳቸውም ቢሮ ይህ ስራ ከግብ እንዲደርስ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በትብብር እንደሚሰሩ ጠቁመዋል። የአስተዳደሩ ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ከድሬደዋ ዩንቨርሲቲ ጋር በተለያዩ አስተዳደራዊ እና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተቀራርቦ እንደሚሰራ በመጠቆም ቅርሶችን ለማጥናት፣ ለመጠበቅ እና አለም አቀፍ እውቅና እንዲያገኙ ለማስቻል የተጀመረውን ስራ ቢሯቸው እንደሚያግዝ አስረድተዋል።
Share This News