ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ከከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር፣ ከከተሞች ገቢ ሪፎርም ፕሮጀክት ጽ/ቤት ጋር በመተባበር እየተሰጠ የነበረው በከተማ መሬት እና ፕላን ዘርፍ የሥልጠና እና የብቃት ማረጋገጫ ምዘና ፕሮጀክት ማጠቃለያ መርሀግብር ተካሄደ።
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም በሀገር አቀፍ ደረጃ በከተማ መሬት እና ፕላን ዘርፍ ያለው የመልካም አስተዳደር ብልሹ አሰራርን ማሻሻል የመንግስት ትኩረት መሆኑን በማስታወስ፣ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም የዘርፉን ባለሞያዎች እዉቀት እና ክህሎት ለማጎልበት የተለያዩ ፕሮግራሞችን በመቅረጽ ተግባራዊ ማድረግ ላይ መሆናቸውን የገለጹ ሲሆን በዘርፉ የስልጠና እና ምዘና አገልግሎት መሰጠቱ በስፋት የሚስተዋለውን የመሬት አስተዳደር ችግር ለመፍታት ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረው ጠቁመዋል።
የዩንቨርሲቲው ፕሬዝዳንት በማከልም የከተማዎች ልማት ለሀገር ኢኮኖሚ የማይተካ ሚና እንዳላቸው በማንሳት፣የከተማ መሬት ይዞታ ምዝገባና መረጃ ስርዓትን በማዘመን በከተሞች ከመሬት አስተዳደር ጋር ተያይዞ የሚታዩ ችግሮችን መቅረፍ፣ በፕላን እንዲመሩ ማድረግና የከተማ መሬት ይዞታ ማረጋገጥና በመመዝገብ፤ ከተሞች ያላቸውን የመሬት ሀብት በአግባቡ እንዲያቁና እንድጠቀሙ፤ እንድሁም ከተሞች ሀብቶቻቸውን በአግባቡ እንድያስተዳድሩ ማስቻል የስልጠናው ዋና አላማ መሆኑን አብራርቷል።
ለዚህም አላማ ድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ከ450 በላይ የሚሆኑ የዘርፉ ባለሞያዎችን ማሰልጠኑን እና ከዚህ በፊትም የዘንድሮ ምዘና ዉጤት ሳይካተት በ 3 ዙር ሰልጥነው ብቁ የሆኑ 254 ባለሞያዎችን ማፍራት መቻሉን አስታዉቀዋል። ለዚህ ዉጤታማ ተግባርም የተሳተፉ የዩኒቨርሲቲው መምህራን እና የአስተዳደር ሰራተኞች ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት ተናቦ በመስራት የዚህ ስልጠና አላማ እንዲሳካ የበኩላቸውን ድርሻ ለተወጡ አካላት በሙሉ የላቀ ምስጋናቸውን አቅርቧል።
በስልጠናው መዝጊያ ስነ-ሥራዓቱ ላይ የተገኙት የኢ.ፍ.ድሪ ከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ድዔታ ክቡር አቶ ፋንታ ደጀኔ የስልጠናውን ፋይዳ አጽንዖት ሰጥተው አብራርተዋል። ክቡር ሚኒስትር ድዔታው በማከልም ሰልጣኞች በየደረጃው ብቁ እንዲሆኑ የስልጠናውን ፋይዳ የዘረዘሩ ሲሆን በተለይም መሪ መዘኞችን በሀገር ውስጥ ማፍራት መቻሉ እና ከውጭ የሚመጡ መሪ መዘኞችን ማስቀረት በመቻሉ ስልጠናውን ልዩ ያደርገዋል ሲሉ ተናግረዋል። መሰልጠን ማወቅ ነው፣ማወቅ ደሞ መለወጥ ነው ያሉት ክቡር ሚኒስቴር ዳኤታው ሰልጣኞች በመሬትና በፕላን ዘርፍ የተቀረጹ ፖሊሲዎችን ፣ ስትራቴጂዎችንና እቅዶችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ በታማኝነት ድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስቧል። በሞያዊ ክፍተት ምክንያት መንግስትንና ህዝብን ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈሉ ያሉ እንደ ፕላን ጥሰት፣የመረጃ ማዛባት፣ የግመታ ስህተትና ሌሎችን በመቀነስ በማስቀረት የህዝብን ጥቅም ማስጠበቅ ይኖርብናል በማለት መልክታቸውን አስተላልፈዋል።
የዘንድሮው ስልጠና በ5 የስለጠና አይነቶች ከአራት ክልሎች ማለትም ከድሬደዋ፣ ሶማሌ፣ አፋር እና ሀረሪ ክልሎች የተውጣጡ 137 ሰልጣኞች ስልጠናውን ወስደው ለምዘና ብቁ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ የስልጠናው ዋና አስተባባሪ አቶ አማን ሁሴን ናቸው።
በስልጠናው ተካፋይ የነበሩ ሰልጣኞች በበኩላቸው ያገኘነው ስልጠና በቀጣይ ለማኅበረሰባቸን ፈጣንና ተቀላጠፋ አገልግልት ለመስጠት ያስችለናል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ሰልጣኞቹ በተለይ የድሬደዋ ዩንቨርሲቲ አመራር፣ አሰልጣኞች እና አስተባባሪዎች ላደረጉላቸው መልካም አቀባበል እና የተሳካ የትምህርት ጊዜ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
Share This News