Logo
News Photo

የ2018 በጀት ዓመት የ6ወር እቅድ አፈፃፀም ሪፓርት ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ቀርቦ ውይይት ተካሄደ

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ባለፉት ስድስት ወራት የተከናወኑ የእቅድ አፈፃፀሞችን ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በማቅረብ ሰፊ ውይይት አድርጓል፡፡ ውይይቱ በዋናነት በበጀት ዓመቱ ሊሰሩ ታቅደው ባለፉት ስድስት ወራት የተሰሩ አንኳር ተቋማዊ ስራዎች፣ ያጋጠሙ ችግሮች እና ችግሮችን ለመፍታት የተከወኑ ተግባራትን በሰፊው ዳሷል፡፡ 

 በዚሁ መድረክ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም እንደተናገሩት የትምህርት ዘርፉን ስብራት ለመጠገን እንደ ሀገር የተያዙ እቅዶችን ከማሳካት አንፃር የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የሚጠበቅበትን ሀላፉነት እንዲሁም ሀገራዊ ተልዕኮ በተገቢው መንገድ ለመፈፀም በርካታ ዝርዝር ተግባራትን እየሰራ መቆየቱን ጠቁመዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በበጀት ዓመቱ ሀገራዊ ተልዕኮዎችን እና የለውጥ ስራዎችን ከመፈፀም አንፃር ብርቱ ጥረት አድርጓል ያሉት ዶ/ር ኡባህ አደም ‘’ዛሬ የሚቀርበው ሪፓርት ተቋሙ የተሰጡትን ተልዕኮዎች ከመፈፀም አኳያ ማሳካት የተቻለውን ውጤት እንዲሁም የተስተዋሉ ድክመቶች ለመለየት ይረዳል’’ ብለዋል፡፡ 

በተቋም ደረጃ የተጀመሩ የለውጥ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ያስገነዘቡት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት የመማር ማስተማር ስራዎችን ከማዘመን፣ ችግር ፈቺ ምርምሮችን እንዲሁም ተጨባጭ መፍትሄ ሰጪ የማህበረሰብ አገልግሎቶችን ከመከወን፣ ከተቁሙ አልፎ ለሀገር የሚተርፉ ቴክኖሎጂዎችን የማበልፀግ ፣ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ምቹ የስራ እንዲሁም የመማር ማስተማር ከባቢን ከመፈጠር፣ ሰራተኞችን የሚያግዙ አገልግሎቶችን ከማስጀመር እንፃር ዩኒቨርሲቲው ሰፊ ጥረቶችን ማድረግ መቻሉን አመላክተዋል፡፡

Share This News

Comment