Logo
News Photo

ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን "እኔ የእህቴ ጠባቂ ነኝ" በሚል መሪ ቃል በፓናል ውይይት በድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ተከበረ፡፡

"እኔ የእህቴ ጠባቂ ነኝ" በሚል መሪ ቃል የዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን (MARCH 8) ዛሬ በድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ የተከበረ ሲሆን በዚሁ በዓል ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም እንደገለጹት ሴቶች ለዘመናት በተዛቡ አስተሳሰቦች ሳቢያ ለተለያዩ ወስብስብ ችግሮች ተጋልጠው ቆይተዋል፡፡  

ምንም እነኳን ይህን በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጫና ለመቀነስ በርካታ ጥረቶች መደረጋቸው ባይካድም እነዚህ ጥረቶች ትርጉም ባለው መልኩ የሴቶችን ችግር ቀርፈዋል ብሎ ለመናገር ያስቸግራል ብለዋል፡፡ 

ሴቶች ያሉባቸው ችግሮች በዘላቂነት ተቀርፈው በሁሉም መስክ ተጣቃሚነታቸውን እና ተሳታፊነታቸውን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ራሳቸው ሴቶች ችግሮቻቸው እንዲፈቱ በፊትአውራሪነት ተሰልፈው የበኩላቸውን መወጣት ይኖርባቸዋለ ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው የሴቶችን ችግር ከመፍታ አንፃርም በአሁኑ ሰዓት ልጅን ተንከባክቦ ለማሳደግ ሴቶች ላይ ከፍተኛ ጫና መፈጠሩን ከግምት ውስጥ በማስገባት በቅርቡ የህፃናት ማቆያ መዕከል ግንባታ መጀመሩን ዶ/ር ኡባህ ጠቁመው ይህ የህፃናት ማቆያ ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እስኪጀምር ድረስም በጊዜያዊነት በዩኒቨርሲቲው የተወሰኑ ክፍት የህንፃ ክፍሎችን ምቹ በማድረግ አገልግሎቱን በማስጀመር የሴቶችን ውጤታማነት ለማሳደግ ጥረት አንደሚደረግ ገልፀው ለዙሁ ስኬትም ሁሉም አካል የበኩሉን ይወጣ ዘንድ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡ 

የድሬደዋ ሴቶች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ክብርት ወ/ሮ ኢፍቱ አባስ በዚሁ ወቅት እንዳሉት እኛ ሴቶች የሚደርስብንን ጫና እና ተፅእኖ ተቋቁመን በተሰማራንበት መስክ ውጤታማ መሆን ይጠበቅብናል ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የሴቶችና ወጣቶች፣ ኤች.አይ.ቪ /ኤድስ/ እና ልዩ ፍላጎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ይታገሱ ፍቃዱ በበኩላቸው ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትና ተሳታፊነት ለማሳደግ ከራሳቸው ከሴቶች ብዙ ይጠበቃል ሴቶች በትምህርት እና በእውቀት አቅማቸውን በየጊዜው በማጎልበት ተለዋዋጭ በሆነው ዓለም ውስጥ ተወዳዳሪነታቸውን ማሳደግ አለባቸው ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡ 

የዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን (MARCH 8) በማስመልከት በተከበረው በዓል ላይ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማጎልበት ያሉ ተስፋዎችና ሊያጋጥም የሚችሉ ተግዳሮቶች በሚል ርዕስ በመምህር ቅድስና ሰብስቤ ጥናታዊ ጽኁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡  

በመጨረሻም በበዓሉ ላይ የተገኘውን  ታዳሚ የሚያዝናኑ የተለያዩ ዝግጅቶች የቀረቡ ሲሆን በዩኒቨርሲቲው ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ያሉና በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ ለቻሉ ሴት ተማሪዎች የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቷል፡፡


Share This News

Comment