ዓለም አቀፉ የምህንድስና ቀን በበርካታ ኩነቶች ታጅቦ በድምቀት ተከብሮ ዋለ፡- መድረኩ የተለያዩ የምህንድስና ውጤት የሆኑ ማሽኖች ቀርበውበታል፣ ቁልፍ መልዕክቶችም ተላልፈዋል
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ዓለም አቀፉን የመህንድስና ቀን በደማቅ ሁኔታ አክብሯል፡፡ በዓሉ የምህንድስና እውቀት ውጤት የሆኑ የተለያዩ ማሽኖች በዩኒቨርሲቲው መምህራን እና ተማሪዎች የቀረበበት ሲሆን ከተለያዩ ተቋማት የመጡ በምህንድስናው ዘርፍ ስመጥር የሆኑ ምሁራን ገለጻ አድርገውበታል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ፋሽን ዲዛይን ትምህርት ቤትም በመምህራን እና ተማሪዎች የተዘጋጁ ዘመናዊ እና ባህላዊ አልባሳትን በማዘጋጀት እንዲሁም የአልባሳት ትርዒት (Fashion show) በማቅረብ ተሳትፎ አድርገዋል፡፡
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም በዚሁ መድረክ ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉ ሲሆን በንግግራቸውም የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ጥራት ያለው የምህንድስና ትምህርትን ከመስጠት አንጻር፣ በሀገር ደረጃ ትልቅ ተፅዕኖ መፍጠር የቻሉ እንዲሁም ለዲጂታል 2025 ስኬት የጎላ አስተዋፅኦ የነበራቸው ዲጂታል ስርዓት (digital systems) ለተለያዩ ክልሎች እና የፌደራል መስሪያ ቤቶች በማበርከት እንዲሁም የኮሪደር ልማት ስራዎችን ጨምሮ በርካታ ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ ምሁራንን በማሳተፍ ዩኒቨርሲቲው ከመንግስት እና ህዝብ የተሰጠውን ተልዕኮ ለመወጣት ሰርቷል ብለዋል፡፡
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ግርማ ቤካ በበኩላቸው በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ከ30 ቢሊዮን ዶላር በላይ በጀት የተመደበላቸው ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች እንደሚኖሩ ጠቁመው እነዚህን ሜጋ ፕሮጀክቶች በስኬት ለማጠናቀቅ እና ለማስተዳደር የመሐንዲሶች እውቀትና ቁርጠኝነት ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡
Share This News