የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ 3 ፕሮጀክቶችን አስመርቆ ለማህበረሰብ አገልግሎት ክፍት አደረገ
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰቡን ችግር የሚፈቱ፣ ለ 50 ሰዎች የሰራ እድል የሚፈጥሩ፣ በጎ አድራጊ ተቋማትን የሚደግፉ እና ወንጀልን በመከላከል ስራዎች ላይ በጎ ተጽዕኖ መፍጠር የሚችሉ 3 የተለያዩ ፕሮጀክቶችን አስመርቆ ለተጠቃሚዎች ክፍት አድርጓል፡፡
ሶስቱን የማህብረሰብ አገልግሎት ስራዎች መርቀው የከፈቱት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም ባስተላለፉት መልዕክት ‘’የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ከሚሰራቸው በርካታ የለውጥ ስራዎች ባሻገር የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ እንዲሁም ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት የሚችሉ የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎችን በትኩረት እየሰራ ነው’’ ብለዋል፡፡
በዛሬው እለት ከተመረቁት ስራዎች ውስጥ አንዱ የሆነው ዘመናዊ የታክሲ ተርሚናል በዩኒቨርሲቲው ዋና መግቢያ በር አካባቢ የሚስተዋለውን የትራፊክ መጨናነቅ ከማስቀረቱም ባሻገር በተርሚናሉ ውስጥ በተገነቡ የመገበያያ ሱቆች እና የንግድ ስፍራዎች አማካኝነት ለ50 የአካባቢው ነዋሪ የስራ እድል የሚፈጥር ለማወቅ ተችሏል፡፡
ሌላኛው በዛሬው እለት የተመረቀው የማህበረሰብ ፓሊሲንግ ማዕከል ሲሆን ማእከሉ ወንጀልን አስቀድሞ ለመከላከል፣ ወንጀለኞችን በህግ ጥላ ስር ለማዋል እንዲሁም በፀጥታ ስራዎች ላይ ማህበረሰቡን ተሳታፊ ለማድረግ እንደሚያግዝ ተነግሯል፡፡ በገንደ ተስፋ አካባቢ የተገነባው ይህ ማዕከል ዘመናዊ ቢሮ፣ የተጠርጣሪ ማቆያ እና የመፀዳጃ አገልግሎት ምስጠት የሚያስችል ነው፡፡
ሶስተኛው በዛሬው እለት የተመረቀው ፕሮጀክት ለአሰገደች አረጋዊያን ማዕከል የተገነባው ሶላር ታዳሽ የሀይል ማመንጫ ሲሆን ፕሮጀክቱ ለአረጋዊያን ማዕከሉ አማራጭ የሀይል አቅርቦት በመፈጠር እንደሚያግዝ ተጠቁሟል፡፡
Share This News