የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ለምዕራብ ሐረርጌ ዞን ትምህርት ቤቶች የኮምፒተር ድጋፍ አደረገ
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ምዕራብ ሐረርጌ ዞን ስር ለሚገኙ ትምህርት ቤቶች የሚውሉ 50 አዳዲስ ኮምፒተሮችን ድጋፍ አደረገ።
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም 6.7 ሚሊየን ብር ግምት ያላቸውን 50 አዳዲስ ኮምፒተሮች ለምዕራብ ሐረርጌ ዞን አመራሮች እንዲሁም ድጋፉ ለተደረገላቸው የትምህርት ቤት ዳይሬክተሮች አስረክበዋል።
ዶ/ር ኡባህ አደም በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት ´´የዲጂታል ኢትዮጲያ 2030 እቅዶች እንዲሳኩ እንዲሁም ተማሪዎች በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሳሉ መሰረታዊ የዲጂታል እውቀት እንዲኖራቸው የትምህርት ቤቶችን የኮምፒተር ቤተ-ሙከራዎች ማደራጀት አስፈላጊ ነው´´ ብለዋል፡፡
ለምዕራብ ሐረርጌ ዞን የተደረገው ድጋፍ በዞኑ ስር የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት ለማሟላት ያለመ ነው ያሉት ዶ/ር ኡባህ ድጋፉ ተማሪዎች በተግባር የተደገፈ የዲጂታል እውቀት እንዲቀስሙና የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ሀገራዊ ጥረት የሚያግዝ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የምርምር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ተማም አወል በበኩላቸው ድጋፉ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የዲጂታል ልማት ስራዎች ላይ የሚያደርገውን ጉልህ አበርክቶ ይበልጥ የሚያጠናክር ነው = ብለዋል፡፡
የምስራቅ ሐረርጌ ዞን አስተዳዳሪ ወ/ሮ ኢክራም ጠሃ በበኩላቸው የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ያደረገው ድጋፍ በዞኑ ስር የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን በእጅጉ ከማገዙም በላይ መንግስት በ2018 ዓ/ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ የመውጫ ፈተና በተመረጡ ሁለተኛ ደረጃ ት/ርት ቤቶች ለመስጠት ያቀደው እቅድ እንዲሳካ ያግዛል ብለዋል፡፡
Share This News