የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል ግንባታን በ18 ወራት በማጠናቀቅ ስራ እንዲጀምር ለማስቻል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ።
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ከድሬዳዋ አስተዳደር የተረከበው የሪፈራል ሆስፒታል የማጠናቀቂያ ግንባታ ደረጃ በአስተዳደሩ ከንቲባና አመራሮች ተጎብኝቷል።
በ2002 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረው የድሬዳዋ ሪፈራል ሆስፒታል ከ10 አመታት በላይ የፈጀ ግንባታው በተለያዩ ምክንያቶች ሲጓተት ቆይቶ አስተዳደሩ ለድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በማስረከብ ግንባታውን እንዲያጠናቅቅና ለማስተማሪያ ሆስፒታልነት ጭምር እንዲውል በ2012 ዓ.ም ማስተላለፉ ይታወሳል።
ይህን ረጅም ጊዜ የወሰደ የሆስፒታል ግንባታ ለማጠናቀቅ ከ290 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በማስመደብና የዲዛይን ማሻሻያ በማድረግ ግንባታውን ቀሪ ስራዎች እየከወነ መሆኑን የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም ይገልጻሉ።
ዶ/ር ኡባህ እንደሚናገሩት ለሆስፒታሉ ግንባታ ዘንድሮ በተያዘለት በጀት የኤሌክትሮ ሜካኒካልና ቀሪ የግንባታ ስራዎችን ለመፈጸም ከተያዘለት የ18 ወራት ጊዜ ገደብ በ3 ወራት ውሥጥ ከ10 በመቶ በላይ በከወኑን ጠቅሰው ከግንባታ ግብዓት የዋጋ ንረት ጋር በተያያዘ የሚገጥሙ ችግሮችን በአፋጣኝ እልባት በመስጠትና በተያዘው ጊዜው ገደብ ለመፈጸም ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
የዩኒቨርሲቲው ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር በወቅቱ እንደገለጹት ድሬዳዋን ጨምሮ ለምስራቁ የኢትዮጵያ ክፍል የሪፈራል ህክምና ለመስጠት ታቅዶ ግንባታው የተጀመረው ይህ ማዕከል የተጓተተ ግንባታው በአግባቡ እንዲጠናቀቅና ዩኒቨርሲቲው ያደረገውን ጥረትና አሁን የሚገኝበት የማጠናቀቂያ ስራ አበረታች መሆኑን ገልጸዋል።
ሆስፒታሉ የማጠናቀቂያ ግንባታው አልቆ ለነዋሪው ግልጋሎቱን በአጭር ጊዜ እንዲጀምር ለማስቻል አስተዳደሩ ለዩኒቨርሲቲው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አቶ ከድር አረጋግጠዋል።
የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ኢዛና አቀሎ በወቅቱ እንደገለጹልን የሆስፒታሉ ግንባታ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ከመፈጸም አኳያ የግብዓት ዋጋ ማሻቀብና እጥረት ከፍተኛ ተግዳሮት እንደሆነ ገልጸው ፕሮጀክቱን በወቅቱ ለማጠናቀቅ ለአገልግሎት እንዲውል ለማስቻል በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
በምልከታው የአስተዳደሩ ከንቲባን ጨምሮ በምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ፣የካቢኔ አባላት፣የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንትና ም/ፕሬዝዳንቶችና አመራሮች ተገኝተዋል።
Share This News