Logo
News Photo

የአለም የአካባቢ ቀን "አንድ ምድር ብቻ" በሚል መሪ ቃል በድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ በፓናል ውይይት ተከበረ፡፡

ዘንድሮ በአለም አቀፍ ደረጃ ለ49ኛ ጊዜ በሀገራችን ደግሞ ለ29 ጊዜ የተከበረውን የዓለም የአካባቢ ቀንን ምክንያት በማድረግ የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲና የድሬደዋ አስተዳደር አካባቢ ፣ደን እና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን በመተባበር  የፓናል ውይይት  አካሂደዋል፡፡

በዚሁ የፓናል ውይይት ላይ በዩኒቨርሲቲው የማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ዲን የሆኑት ዶ/ር አለማየሁ ዘውዴ ባደረጉት የእንኳን ደህና መጣቹህ ንግግራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ መጠን እየጨመረ የመጣው የከባቢ አየር ሙቀት መጨመርና የአካባቢ ብክለት    የምድራችን ህልውና ቀጣይነት  ላይ ጥያቄ የፈጠረ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡

 አሁን ባለንበት ዘመን  ወደ ከባቢ አየር የሚለቁት በካይ ጋዞች መጨመር ፤ የአካባቢ ብክለት እና የተፈጥሮ ሀብቶች ውድምት  በመድራችን ላይ የአየር ንብረት ለውጥን እንዲከሰት በማድረግ  የተፈጥሮ አደጋዎች ከቀደመው ዘመን በእጅጉ በበለጠ መጠን በተደጋጋሚ እንዲከሰቱ እና  ለብዙዎች እልቂት፣ጉዳት እና ከቀዬ መፈናቀል ምክንየት እንዲሆኑ እያደረገ ይገኛል፡፡

ይህ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚከሰት የተፈጥሮ አደጋ የሚያስከትለው ጉዳትና ተጽኖ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ ሀገራት ላይ የሚፈጥረው ጫና የበረታ ነው ያሉት ዶ/ር አለማየሁ የተፈጥሮ ሀብታችንን በመንከባከብ መድራችን ለሰው ልጆችና ለመላው  ህይወት ላለው ፍጡር ሁሉ  ምቹ መኖሪያ መሆን እንድትችል ተቀራርቦና ተቀናጅቶ  የመስራት ጅምር ልምዳችን ልናጎለብተው ይገባናል ብለዋል፡፡

"ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በድሬደዋና በአካባቢው ለውጥና እድገት እንዲመጣ ከፍተኛ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ከሚገኘው ከድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ጋር ተቀራርበን መስራት መቻላችን የተፈጥሮ ሀብታችን በመንከባከብ የአየር ንብረት ለውጥ እያመጣ ያለውን ጉደትና ተጽእኖ ለመቋቋም የጀመርናቸውን ተግባራት ዳር ማድረስ እንድንችል ትልቅ አቅም ይፈጥርልናል" ያሉት የድሬደዋ አስተዳደር አካባቢ ፣ደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ስራ አስኪያጅ አቶ አብዱ መሐመድ አባመጋል ናቸው፡፡

" መድራችን ስተፈጠር ተፈጥሯዊ ሚዛኗን ጠብቃ ሙሉ ሆና የተፈጠረች ቢሆንም አሁን ባለንበት ዘመን ግን እኛ የሰው ልጆች ተፈጥሮ ላይ ባደረሰውነው ጥፋትና ውድመት የምድራችን ተፈጥሯዊ  ሚዛን ተዛብቶ  ለመጥፋት እንድትቃረብ አድረገናታል" ያሉት አቶ አብዱ አሁን የተጋረጠብን ከፍተኛ አደጋ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ሁላችንም ተባብረን ለራስችን ስንል አለማችን ከጥፋት ልንታደጋት ይገባል ብለዋል፡፡

እንደ ድሬደዋ አስተዳደርም የተፈጥሮ ሀብታችንን በመንከባከብ  የአየር ንብርት ለውጥ እያስከተለ ያለውን ከፍተኛ ጫና  ለመቋቋም የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ በተለይ በጥናትና ምርምር ስራዎች  የሚኖረው እገዛ ከፍተኛ በመሆኑ የጀመረውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ ይቀጥል ዘንድ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡ 

"አንድ ምድር ብቻ" በሚል መሪ ቃል ለአንድ ቀን በቆየው የፓናል ውይይት ላይ በድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ዮናስ ታደሰ የአየር ንብረት ልወጥ መንስኤዎች፣ እየሳከተሉት ያለው ጉዳት በተለይም ማህበራዊ ፣ምጣኔሀብታዊ እና ፓለቲካዊ ተፅእኖዎቻቸው ላይ ትኩረት ያደረጉ ጥናታዊ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡


Share This News

Comment