Logo
News Photo

አራተኛው ዙር ሴሚናር በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ተካሄደ፡፡

በሴሚናሩ ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው የምርምር ህትመት፣ ስነዳና ስርጭት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር መሐመድ ቃሶ ሲሆኑ በንግግራቸውም የዚህ አይነቱ ሴሚናር ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ በኮሌጅ ደረጃ ይካሄድ የነበረ መሆኑን አስታውሰው የዛሬው ሴሚናር በ2014 ዓ.ም በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ለአራተኛ ጊዜ የተካሔደ እንደሆነም ጠቁመዋል። 

እንደ ዶ/ር መሐመድ ገለፃ በዛሬው እለት የቀርቡት የሴሚናር አርዕስቶች ከዚህ በፊት በኮሌጅ ደረጃ በተለያዩ ምሁራን የቀረቡና በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ለአራተኛው ዙር ሴሚናር የተመረጡ መሆናቸውንም ጨምረው ገልፀዋል። 

በእለቱ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም ሲሆኑ በንግግራቸውም 

ዩኒቨርሲቲው ከመቼውም ግዜ በተሻለ መምህራን ሴሚናሮችን እንዲያቀርቡና እርስ በርስ የምንማማርበትን ምቹ የሆነ መደላድልን እየፈጠረ እንደሆነ ጠቁመው መምህራንም ይህንን እድል በመጠቀም በዛሬው እለት ጥናታዊ ፅሁፎቻቸውን በማቅረባቸው አመስግነዋል። 

በመቀጠል በሴሚናሩ ላይ የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሰለሞን ዘሪሁን ንግግር ያደረጉ ሲሆን በንግግራቸውም በዩኒቨርሲቲ ደረጃ በ2014 ዓ.ም አራት ሴሚናሮችን ለማካሔድ እቅድ እንደነበረ አስታውሰው ከዚህ በፊት የተካሄዱት ሦስት ዙር ሴሚናሮች መምህራን ብዙ እውቀት እንዲያገኙ ያስቻሉ መሆናቸውን ጠቁመው ይህ ዛሬ የተካሔደው አራተኛው ዙር ሴሚናርም የዚሁ እቅድ አካል እንደሆነ ተናግረዋል። 

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ዶ/ር ሰለሞን  እንደተናገሩት የም/ማ/አገ/ም/ፕ/ጽ/ቤት ከዚህ በኋላም በትምህርት ክፍል ደረጃ ቢያንስ በየሩብ ዓመቱ አንድ ግዜ ሴሚናር እንዲካሄድ እቅድ እንዳለው ጠቁመው ይህንንም ተፈፃሚ ለማድረግ ጽ/ቤቱ  አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደረግ ተናግረዋል ። 

በዚህ ለግማሽ ቀን በቆየው ሴሚናር ላይ አራት ጥናታዊ ጽሁፎች በዩኒቨርሲቲው መምህራን 1. በዶ/ር  አሸናፊ ተስፋዬ ከማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ፣ 2. በመ/ር በየነ አቢቲ ከተፈጥሮና ኮምፒውቴሽናል ሳይንስ ኮሌጅ፣ 3. በረ/ፕ ዮናታን ሰለሞን ከህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ እንዲሁም 4. በመ/ር መኮንን መገርሳ ከቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ቀርበው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን በሴሚናሩ ላይ ቁጥራቸው ከ100 በላይ የሚሆን መምህራን ታድመዋል። 

በመጨረሻም በሴሚናሩ ላይ ጥናታዊ ፅሁፍ ላቀረቡ መምህራን በሴሚናሩ አዘጋጆች የእውቅና ሰርተፍኬት የተሰጠ ሲሆን በ2015 በጀት ዓመትም መምህራን የተሻሉና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ አዳዲስ የመማማርያና የመወያያ ሴሚናሮችን እንዲያዘጋጁ ዶ/ር መሐመድ መልእክታቸውን በማስተላለፍ የእለቱ ፕሮግራም ተጠናቋል።

Share This News

Comment