Logo
News Photo

የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ከ90 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ በጀት ያስገነባው የተማሪዎች ዘመናዊ ከፍተኛ ክልኒክ ተመረቀ፡፡

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ በዩኒቨርሲቲው የቢዝንስ ልማት ም/ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶ/ር ተማም አወል እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው የተማሪዎችን የህክምና አገልግሎት ሽፋን የጥራት ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ለማሳደግ አቅዶ ባለፈው 2011 ዓ.ም ነሃሴ ወር ላይ ጥላሁን አበበ ከተሰኘ ጠቅላላ የህንፃ ተቋራጭ እንዲሁም አኪዩት ከተባለ አማካሪ ድርጅት ጋር በገባው ውል መሠረት ግንባታው ተጀምሮ ዛሬ ለምረቃ መብቃቱን ገልፀዋል፡፡

ከፍተኛ ዘመናዊ ክሊኒኩ እስካሁን 78 ሚሊየን ብር ወጪ የተደረገበት ሲሆን በአሁኑ ሰዓትም 89 በመቶ የሚሆነው ስራ መጠናቀቁ እና ቀሪውን 10 በመቶ የሚሆነውን ስራም በጥቂት ጊዜ ውስጥ አጠናቆ አገልግሎቱን ለማስጀመር ጥረት እንደሚደረግ ዶ/ር ተማም በዚሁ ወቅት ተናግረዋል፡፡

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት  የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች አገልግሎትና አስተዳደር ጉዳዮች ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር አብርሃም እውነቱ በበኩላቸው የዚህ ከፍተኛ ዘመናዊ ክሊኒክ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆን ከዚህ ቀደም የተሟላና በሚፈለገው ደረጃ ለተማሪዎች የህክምና አገልግሎት ለመስጠት የነበረውን ክፍተት የሚሞላና ከተማሪዎችም አልፎ ለተቀረው የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል በመሆኑ ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል፡፡

ለዚህ ዘመናዊ ከፍተኛ ክሊኒክ መገንባትና ለአገልግልት ዝግጁ መሆን የቀደሙ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ የበርካታ አካላት ርብርብ ውጤት በመሆኑ እነዚህ አካላት ላበረከቱት አስተዋፆኦ ከፍተኛ ምስጋና ይገባቸዋል ያሉት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም ናቸው፡፡

ዶ/ር ኡባህ አክለውም  "ክሊኒካችን  ዘመኑ ባፈራቸው የህክምና አገልግሎት መስጫ መሣሪያዎች ማደራጀት እንድንችል ከፍተኛ ድጋፍ ላደረገልን ሂዩማን ብሪጅ ለተሰኘውን አለም አቀፍ ግብረሰናይ ድርጅት በላቀ ደረጃ ላመሰግን እወዳለሁ ያሉት ዶ/ር ኡባህ በተለይ ይህንን ድጋፍ እንድናገኝ ትልቁን  አስተዋፆኦ ለተወጣው ቅን ልብ ላለውና ለአገር ወዳዱ የድርጅቱ የካንትሪ ዳይሬክተር ለዶ/ር አዳሙ አንለይ ያለኝን ትልቅ ክብርና ምስጋና ላቀርብ እወዳለሁ ብለዋል፡፡   

ሂዩማን ብሪጂ የተሰኘው አለም አቀፍ ግብረሰናይ ድርጅት መቀመጫውን ስዊድን ሀገር ያደረገና በአለም ላይም በተለያዩ አገራት 50 ቅርንጫፎችን ከፍቶ የሚንቀሳቀስ ሰብአዊነት ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ድርጅት ሲሆን ዛሬ ለምርቃ ለበቃው ለድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ዘመናዊ ከፍተኛ ክሊኒክም አጠቃላይ ግምቱ 10 ሚሊየን ብር የሚጠጋ የህክምና አገልግሎት መስጫ መሣሪያዎችን አና የተለያዩ መጠን ያላቸው የሆስፒታል የመኝታ አልጋዎችን ድጋፍ አድርጓል፡፡

የሂዩማን ብሪጂ አለም አቀፍ ግብረሰናይ ድርጅት ካንትሪ ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር አዳሙ አንለይ በዚሁ የምርቃት ስነ-ስረዓት ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር በኢትዮጵያ እስካሁን ከጎበኝዋቸው ዩኒቨርሲቲዎች መካከል በዚህ ደረጃ ላይ የሚገኝ የተማሪዎች ክሊኒክ አለመመልከታቸውን ገልፀው ድርጅታቸው ለክሊኒኩ ተጨማሪ ድጋፎችን እንደሚያደርግና በተለይም ዩኒቨርሲቲው ከድሬደዋ አስተዳደር ተረክቦ ሙሉ ስራውን በማጠናቀቅ ላይ ለሚገኘው የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል ግምቱ ግማሽ ቢሊዮን ብር የሚገመት የህክምና መስጫ መሣሪያዎች ድጋፍ አንድሚያደርጉም ቃል ገብተዋል፡፡ 

ዘመናዊ ከፍተኛ ክሊኒኩ በውስጡ የውስጥ ደዌ፣ የጥርስ፣ የአይን፣ የድንገተኛ፣ ቀላል የቀዶ ጥገ፣ የእናቶችና  የጨቅላ ህፃናት ህክምና እንዲሁም ሌሌችም የህክምና አገልግሎቶች መስጠት በሚያስችሉ የተለየያዩ የህክማና ክፍል የተደራጀ መሆኑን በምርቃት ስነ-ስርዓቱ ላይ ተገልፃል፡፡

Share This News

Comment