Logo
News Photo

በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ሦስተኛው ዙር የተጠናቀቁ የምርምር ስራዎች የግምገማ መድረክ ላይ ከ50 በላይ የተጠናቀቁ የምርምር ስራዎች ቀረቡ፡፡

በግምገማ መድረኩ መክፈቻ ላይ በመገኘት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሰለሞን ዘሪሁን ሲሆኑ በንግግራቸውም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዩኒቨርሲቲው እየተደረጉ ያሉት የምርምር ስራዎች ከብዛትም ሆነ ከጥራት  አንጻር  በከፍተኛ መጠን ማሳደግ የተቻለበት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

እንደ ዶ/ር ሰለሞን ገለፃ የዩኒቨርሲቲው የምርምር ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት  የአሰራር ስርአቱን  ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ እያዘመነ በመምጣቱና ለምርምር ስራ ማነቆ የሆኑ አካሄዶችን ከዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመነጋገር እየቀረፈ በመምጣቱ ምክንያት የመምህራን በጥናትና ምርምር ስራዎች ያላቸው ተሳትፎ መጨመሩን ጠቅሰው በ2030 ዩኒቨርሲቲው የያዘውን ርዕይ ማሳካት እንድንችል በተለይ በጥናትና ምርምሩ ዘርፍ  የዩኒቨርሲቲው መምህራንና ተመራማሪዎች  የበኩላቸው ድርሻ ይወጡ ዘንድ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

በዚሁ የግምገማ መድረክ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም በበኩላቸው የምርምር ሥራዎችን ሰርቶ ማጠናቀቅ አንድ ስኬት ቢሆንም እነዚህ የምርምር ሥራዎች ጆርናሎች ላይ ለህትመት በቅተውና  ወደመሬት ወርደው የማኅበረሰቡን ችግር መፍታት እንዲችሉ ተመራማሪዎች ጥረታቸውን እስከ ጥግ ድረስ ማደረስ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡

በዚህ ለሁለት ቀን በቆየውና የዩኒቨርሲቲው የምርምር ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ባዘጋጀው የምርምር ሥራዎች የግምገማ መድረክ ላይ ቁጥራቸው ከ50 በላይ የሆኑ ያለቁ የምርምር ስራዎች ቀርበው አስፈላጊው ግምገማና ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን ይህም በዩኒቨርሲቲዉ ታሪክ ከፍተኛው ቁጥርን የያዘ ያለቁ የምርምር ሥራዎች በአንድ መድረክ ላይ የቀረበበት መሆኑን በድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት ረ/ፕሮፌሰር ይታገሱ ስንታየሁ ተናግረዋል።  

በመጨረሻም ረ/ፕሮፌሰር ይታገሱ እንደተናገሩት በቀጣዮቹ ጊዜያት አሁን በዩኒቨርሲቲው መምህራን ዘንድ በምርምር ዙርያ ያለዉን መነቃቃት ይበልጥ በማስቀጠል ችግር ፈቺ የሆኑ የምርምር ውጤቶችን  ለአካባቢዉ ማኅበረሰብ የሚደርስበትን መንገድ ዳይሬክቶሬቱ እንደሚያመቻች ቃል ገብተዋል፡፡


Share This News

Comment