Logo
News Photo

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የከተሞች ገቢ ሪፎር ፕሮጀክት ጽ/ቤት ከድሬድዋ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ከተለያዩ ክልሎች ለተውጣጡ የመሬትና ፕላን ባለሙያዎች የሙያ ደረጃ ምዘናን አስመልክቶ ለ35 ቀናት ሲሰጥ የቆየው ስልጠና ተጠናቀቀ፡፡

በስልጠናው ማጠናቀቂያ ላይ ተገኝተው የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም በሀገራችን መሬትን በዘመነ መንገድ በመምራት እና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እንዲዳረስ በማድረግ በከተሞች እድገትና ለውጥን ማምጣት ያስፈልጋል፡፡

እድገትና ለውጡ እንዲመጣ ካስፈለገም ደግሞ ከመሬትና መሬት ነክ  ከሆኑ ጉዳዮች ጋር በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ግንኙነት ኖራቸው በስራ ላይ የሚገኙ ባለሞያዎች የብቃት ደረጃቸው ተመዝኖ የተረጋገጠ መሆን ይገባል፡፡ ይህን ደግሞ ባለሞያዎቹን በየጊዜው አቅማቸውን በሚገነቡ ስልጠናዎች ማብቃት ያስፈልጋል ያሉት ፕሬዝዳንቷ ዩኒቨርሲቲው በሀገራችን የዘመነና ፍትሃዊ የሆነ የመሬት አስተዳደር እንዲኖር ከሚኒስቴር መስሪያቤቱ ጋር የጀመረውን የጥምረት እንቅስቃሴ አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡

በዚሁ የምዝጊያ ፕሮግራም ላይ በመገኘት ለሰልጣኞቹ የስራ መመሪያና መልዕክት ያስተላለፋት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የከተሞች ገቢ ሪፎር ፕሮጀክት ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ  ወ/ሮ ዚነት ኢብራሒም በዚሁ ወቅት እንዳሉት በሀገራችን መሬት በተለይም የመሬት የመረጃ አሰባበሰብ  እጅግ ኋላቀር በሆነ አግባብ መመራቱ  የዜጎችን የባለቤትነት መብትን ከማረጋጋጥ አኳያ ሰፊ ክፍተት እንዲኖር አድርጎታል፡፡

ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ይህንን ችግር ግምት ውስጥ በማስገባት በተለይ ካለፈው ዓመት ጀምሮ የተለያዩ ህጎችና አዋጆችን በማፀደቅ እንዲሁም አዲስ አደረጃጀት በመዘርጋትና በመተግበር ቀላል የማይባል እንቅስቃሴ ቢያደርግም ከችግሩ ውስብስብነት አንፃር ከታሰበው ደረጃ ላይ መደረስ አልተቻለም ብለዋል፡፡

ይህንም ታሳቢ በማድረግ ሚንስቴር መስሪያቤቱ በዘርፉ ያለውን ክፍተት በመለየትና ከፍተኛ  ትኩረት በመስጠት የተለያዩ ስራዎችን የሰራ ሲሆን በተለይም ባለሞያዎችን ከማብቃት እንፃር ካለፈው 2006 ዓ.ም ጀምሮ በ3 ዙር ከ4 ሺህ በላይ ሙያተኞችን አስልጥኖ በመዘን የችግሩን ክፍተት ለመሙላት የተለያዩ ጥረቶችን አድርጓል፡፡

በቅርቡም በ5 ዩኒቨርሲቲዎች ባለሙያዎች ሰልጥነው እንዲመዘኑ አድረጓል ያሉት ስራ አስኪያጇ ከነዚሁ መካከል የዛሬው የምረቃ ፕሮግራም አንዱ ሲሆን በተለይ የአሁኑ ስልጠና ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ አሰልጣኖች የተሰጠ በመሆኑ ግምቱ ቀላል የማይባል የሀገር ሀብት ማትረፍ የቻልንብትና አቅም የፈጠርንብት ነው ብለዋል፡፡ 

ስለጣኞችም ያገኛችሁትን እውቀት ተጠቅማችሁ ከሌብንትና ከብልሹ አሰራር ራሳችሁን አርቃችሁ በብቃትና በታማኝነት ኃላፊነታችሁን ልትወጡ ይገባችኋል በማለት አስግንዝበዋል፡፡

በመዝጊያ ስነ-ስርዓቱ ላይ ስልጠናው ለተከታተሉ ባለሞያዎች የምስክር ወረቀት የተበረከተላቸው ሲሆን ሰልጣኞች፣ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች እና ተጋባዥ እንግዶች  በተገኙበት በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ጊቢ ለሀገራዊው የአረንጓዴ ልማት አሻራ ዘመቻ መርሀ ግብር የችግኝ ተከላ አከናውነዋል፡፡

Share This News

Comment