Logo
News Photo

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የ2014 ዓ.ም የክረምት የሳይንስ፣ቴክኖሎጂ፣ ምህንድስና እና ሂሳብ (STEM) ፕሮግራም ማስጀመሪያ መርሀግብር አካሄደ፡፡

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ፣ቴክኖሎጂ፣ ምህንድስና እና ሂሳብ (STEM) ማዕከል በድሬዳዋ  አስተዳደር ሥር ከሚገኙ የግልና የመንግስት 1ኛና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በሂሳብና የሳይንስ የትምህርት ዓይነቶች የተሻለ ውጤት እንዲሁም የፈጠራ ዝንባሌ ያላቸውን ተማሪዎች በመመልመል  በተግባር የተደገፈ ሥልጠናዎችን እየሰጠ ይገኛል፡፡ በዚሁ መሰረትም የ2014 ዓ.ም የክረምት ወራት የSTEM ሥልጠና የማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ለስልጠናው የተመለመሉ ተማሪዎች ወላጆቻቸውና የትምህርት ቤት ርዕሰ-መምህራኖች በተገኙበት ተካሂዷል፡፡

ፕሮግራሙን በመክፈቻ ንግግር የከፈቱት የዩኒቨርሲቲው ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝደን ዶ/ር ሰለሞን ዘሪሁን ባስተላለፉት መልዕክት መድረኩ የተዘጋጀው ሰልጣኝ ተማሪዎችና ወላጆች ስለSTEM ፕሮግራም ምንነት፤ ጥቅም፤ አቀራረብና የሰልጣኞችና ወላጆች ሃላፊነት ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር ታስቦ መሆኑን ገልፀው ወላጆች የስልጠናውን ጠቀሜታ በመረዳት የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ አደራ ብለዋል፡፡ አያይዘውም ዩኒቨርሲቲው ሰልጣኝ ተማሪዎቹ ስልጠናውን በትኩረት እንዲከታተሉ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡

የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ወንዲፍራው ደጀኔ በበኩላቸው ፕሮግራሙ ተማሪዎች በሳይንስና ቴክኖሎጂ በተግባር የተደገፈ ስልጠና የሚያገኙበት በመሆኑ የዛሬ ሰልጣኞች ነገ የፈጠራ ባለቤቶች የሚሆኑበትና አገራቸውን በሳይንስና ቴክኖሎጂ ወደፊት የሚያራምዱበትን መሰረት የሚያሲዝ መሆኑን በመገንዘብ ስልጠናውን በንቃት እንዲከታተሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡  

በመጨረሻም የዪኒቨርሲቲው የSTEM ማዕከል አስተባባሪ መ/ር ግዛው ገ/ስላሴ በፕሮግራሙ ላይ ከ7ኛ-12ኛ ክፍል ያሉ ከተለያዩ ት/ት ቤቶች የተውጣጡ ከ100 በላይ ተማሪዎች የሚሳተፉ መሆኑን ተናግረው አጠቃላይ ስለፕሮግራሙ ምንነትና ከተማሪዎችና ወላጆች የሚጠበቀውን በገለፃ መልክ አቅርበዋል፡፡ በፕሮግራሙ ላይ የተገኙ የተማሪ ወላጆችም ዩኒቨርሲቲው ባመቻቸው እድል ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀው ለልጆቻቸው የቅርብ ክትትልና ድጋፍ የሚዲርጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

Share This News

Comment