Logo
News Photo

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የ2014 ዓ.ም. የክረምት የSTEM ፕሮግራም ሲማሩ የነበሩ 1ኛና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን በዛሬው እለት አስመረቀ፡፡

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ፣ቴክኖሎጂ፣ ምህንድስና እና ሂሳብ (STEM) ማዕከል በድሬዳዋ አስተዳደር ሥር ከሚገኙ የግልና የመንግስት 1ኛና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በሂሳብና የሳይንስ የትምህርት ዓይነቶች የተሻለ ውጤት እንዲሁም የፈጠራ ዝንባሌ ያላቸውን ተማሪዎች በመመልመል በተግባር የተደገፉ ሥልጠናዎችን ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ በዚሁ መሠረትም ዩኒቨርሲቲው የ2014 ዓ.ም የክረምት ወራት የSTEM የስልጠና መርሃ-ግብር ውስጥ ታቅፈው ላለፈው 1 ወር ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ ቁጥራቸው 138 የሚሆኑ ተማሪዎችን በዛሬው እለት አስመርቋል፡፡

በስነ-ስርዓቱ ላይ ተገኝተው ለ1 ወር በዘለቀው ስልጠና በትምህርታቸው የላቀ ውጤት ላመጡት ተማሪዎች የማበረታቻ ሽልማት ያበረከቱት የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም ተማሪዎች በሳይንስና ሂሳብ ትምህርቶች ላይ ያላቸውን እውቀት በየጊዜው በማዳበር አዳዲስ የፈጠራ ስራዎችን በመስራት ሀገራችንን ከድህነትና ኋላቀርነት ለማላቀቅ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የራሳቸውን አሻራ ማኖር እንዲችሉ  ከወዲሁ ዝግጅት ማድረግ አለባቸው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በተለይም በንድፈ-ሃሳብ ያገኙትን እውቀት በተግባራዊ ልምምድ በመደጋገምና በመመራመር  ችግር-ፈቺ የሆኑ የፈጠራ ስራዎች ላይ በማተኮር ሀገራችን የጀመረችው የልማትና የእድገት ጉዞ ዳር እንዲደርስ ከወዲሁ ትምህርታቸው ላይ ትኩረት በማድረግ የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሰለሞን ዘሪሁን በበኩላቸው ተማሪዎች በንድፈ-ሃሳብና በተግባር ሲቀስሙ የቆዩትን እውቀት በመጠቀም በቀላሉ በአካባቢያቸው የሚገኙ አገልግልት የማይሰጡ ቁሳቁሶችን በመጠቀም የፈጠራ ስራዎችን በመስራት ከራሳቸው አልፈው ሀገር የሚጠቅሙ ዜጋ መሆን ይጠበቅባቸዋል ፡፡ ለዚህም ደግሞ ዩኒቨርሲቲው በ(STEM) ፕሮግራም ስር ለታቀፉት ተማሪዎች በቻለው አቅም ሁሉ ድጋፉን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን በዚሁ መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር አረጋግጠዋል፡፡

በዚሁ የማጠናቀቂያ ስነ-ስርዓት ላይ የተገኙት በኢ.ፌ.ዴ.ሪ   የትምህርት ሚኒስቴር የማህበረሰብ አገልግሎትን ሃገር-በቀል እውቀት ዴስክ ሃላፊ ወ/ሮ ሰላም ዓለሙ ባደረጉት ንግግር ላይ እንዳመለከቱት ዛሬ ላይ በስልጣኔው ጫፍ መደረስ የቻሉት የዓለም ሀገራት የእድገታቸው አንዱ ሚስጠር ለሳይንስና ቴክኖሎጂው የሰጡት ከፍተኛ ትኩረት አንዱና ዋነኛው  ነው፡፡ በተለይም በሳይንስና ሂሳብ ትምህርቶች የተለየ ዝንባሌ ያላቸውን ህፃናትን ገና ከጅምሩ ፍላጎታቸውን ተረድተው ኮትኩተው ማሳደግ በመቻላቸው ብዙ ሳይንቲስቶችና ተመራማሪዎችን በማፍራት አገራቸውን ማሳደግ ችለዋል፡፡

በእኛም ሀገር መንግስት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለሳይንስና ሂሳብ ትምህርቶች ልዩ ትኩረት በመስጠት በርካታ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲም ይህንን ሀገር የጀመረችውን እንቅስቃሴ የሚደግፍ ስራ በመስራቱ የሚበረታታ በመሆኑ ይህንን የጎላ ፋይዳ ያለው እንቅስቃሴ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

በመጨረሻም ለተማሪዎቹ ትምህርቱን ሲሰጡ የነበሩ መምህራንና ለአንድ ወር የቆየውን ትምህርት በንቃት ለተከታተሉና የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የምስክር ወረቀትና የማበረታቻ ሽልማቶችን ከእለቱ የክብር እንግዶች እጅ ተቀብለዋል፡፡


Share This News

Comment